አፍሪካ
የአፍሪካ ህብረት የጊኒ ቢሳዎን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እንደሚቃወም አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/03/2018፡- የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ በጊኒ ቢሳዎ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱንና ይህንን ተከትሎ ፕሬዝደንት ኡማሮን ሲኮሶ ኢምባሎን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለእስር መዳረጋቸውን አውስቶ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚቃወም ገልጿል፡፡
የህብረቱ ኮሚሽነር መሀመድ አሊ የሱፍ ባወጡት መግለጫ ‹‹ይህ ድርጊት የተፈፀመው አገሪቱ ምርጫ አካሂዳ ውጤቱን እየተጠባበቀች ባለችበት ወቅት ነው›› ያሉ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት ማናቸውንም ህገ መንግስታዊ ያልሆነ የመንግስት ለውጥን እንደማይቀበል አስረድተዋል፡፡
ምርጫውን በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች በስፍራው ተገኝተው መመልከታቸውንና ትላንት ሪፖርት ማቅረባቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ በአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የምርጫው ውጤት ይፋ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በህገ መንግስቱ የምርጫውን ውጤት ይፋ የማድረግ ስልጣን የተሰጠው ኮሚሽን የሚያቀርበውን ውጤት ማክበር አስፈላጊና ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ጨምረውም የታሰሩት ፕሬዝደንትና ሌሎች ባለስልጣናት በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ሁሉም አካላት ሁኔታው እንዳይባባስ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት ወታደራዊ መኮንኖች ትላንትና የሽግግር ፕሬዝዳንት መሾሟቸው ተገልጿል።



