የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአሁኑ ሰዓት ከዩክሬን ጋር የሰላም ስምምነት መፈረም “በህጋዊ መንገድ የማይቻል መሆኑን አስታወቁ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/03/2018፡- ፕሬዝዳንት ፑቲን በሰጡት መግለጫ ሞስኮ በመጨረሻ ስምምነት ላይ መድረስ ብትፈልግም፣ አሁን ያለው የዩክሬን አመራር ምርጫ በመሰረዙ ምክንያት “ሁሉንም ህጋዊነት አጥቷል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በኪርጊስታን ያደረጉትን የመንግስት ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ባደረጉት ንግግር “ከዩክሬን አመራር ጋር ሰነዶችን መፈረም ምንም ትርጉም የለውም፣ይህንን ርዕስ ብዙ ጊዜ አንስቼዋለሁ” ብለዋል።
እንደ ሩሲያው ፕሬዝዳንት ገለጻ “የዩክሬን አመራር ምርጫ ለማካሄድ በመፍራት መሰረታዊ እና ስትራቴጂካዊ ስህተት ሰርቷል።” በዚህም ምክንያት የዩክሬኑ መሪ ቮሎዲሚር ዜለንስኪ “ህጋዊ የፕሬዝዳንትነት ደረጃቸውን አጥተዋል” ሲሉ ፑቲን ተናግረዋል።
በዩክሬን ህግ መሰረት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መካሄድ የነበረበት በግንቦት 2024 ነበር። ሆኖም ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ “የማርሻል ህግን” (የጦር ጊዜ አዋጅን) በመጥቀስ ምርጫውን ለማካሄድ ፈቃደኛ አልሆኑም። ሞስኮ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዜለንስኪን “ህጋዊ መሪ አይደሉም” የሚል አቋም ይዛለች።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ እራሷ በወታደራዊ ግጭት ውስጥ ብትሆንም፣ በመጋቢት 2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማካሄዷን በማነፃፀሪያነት አንስተዋል።
ማንኛውም የሰላም ስምምነት ቢፈረም፣ የዩክሬን አመራር “የማርሻል ህግን አንስቶ ወዲያውኑ ምርጫ መጥራት” እንደሚኖርበት የገለጹት ፑቲን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን “የዩክሬን አመራር ምርጫውን ሳያጭበረብር በምርጫ ድል ያገኛል ብሎ ማሰብ ይከብዳል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ፑትን እንዲህ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በዩክሬን ያለውን ግጭት ለማስቆም ያለመ የሰላም እቅድ ማዕቀፍ እያቀረበ ባለበት ወቅት ነው።



