በጊኒ ቢሳዎ ምርጫ ከተካሄደ ከሦስት ቀናት በኋላ ወታደሮች ሥልጣን መቆጣጠራቸውን አስታወቁ፡፡
የጊኒ ቢሳዎ ወታደሮች በአገሪቱ የፕሬዝዳንት ምርጫ ከተካሄደ ከሦስት ቀናት በኋላ ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ስር አውለው መላዋ አገሪቱን መቆጣጠራቸውን አስታወቁ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 18/03/2018፡- የጦር መኮንኖቹ ፕሬዝዳንት ኦማሮ ሲሶኮ ኤምባሎን መያዛቸወን ያስታወቁት ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በዋና ከተማዋ ቢሳዎ በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ከባድ ተኩስ ከተሰማ በኋላ ነው።
ወታደሮቹ እሁድ ዕለት የተካሄደው እና ወጤቱ ዛሬ ይታወቃል ተብሎ እየተጠበቀ የነበረውን የምርጫ ሂደት በማገድ ሁሉንም የአገሪቱን ድንበሮችን እንዲዘጉ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
የፕሬዝዳንቱ መታሰር እና የወታደራዊ አመራሮች ሥልጣን መያዝ የተሰማው በአገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ዋነኛው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከውድድር ውጪ መደረጋቸው ከተሰማ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንት ኡማሮ ሲስኮ ኤምባሎ እንዲሁም ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ፈርናንዶ ዲያዝም በምርጫው እንዳሸነፉ ገልጸዋል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደዘገበው፤ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእግራቸው እንዲሁም በመኪና ሸሽተዋል።
ሥልጣን የተቆጣጠሩት ወታደራዊ መኮንኖች ኋላ ላይ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው “ሥርዓት አስከባሪ ከፍተኛ ወታደራዊ ዕዝ” የተባለ አካል ተጨማሪ መግለጫ እሰኪሰጥ ድረስ አገሪቱን እንደሚመራ አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት ወታደሮች በተጨማሪም ሕዝቡ “እንዲረጋጋ” አዝዘዋል።
በወታደሮቹ ቁጥጥር ስር የዋሉት ፕሬዝዳንት ኦማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ በምርጫው ለሁለተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን የተወዳደሩ ሲሆን፣ እርሳቸውም ሆኑ ተፎካካሪያቸው ውጤቱ ከመታወቁ በፊት አሸናፊ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
ጊኒ ቢሳዎ ከቅኝ ግዛት ከወጣች በኋላ ተደጋጋሚ መፈንቀለ መንግሥት እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲያጋጥማት ቆይቷል።
በፖርቹጋል ቅኝ በተገዛችው ጊኒ ቢሳዎ ከአወሮፓውያኑ 1980 ወዲህ ዘጠኝ መፈንቅለ መንግሥቶች ተካሂደዋል።



