በኢራን በኬሚካል ጭስ ምክንያት በዓመት ከ58 ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 16/03/2018፡- በኢራን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ከሚቃጠል ማዙት ከሚባል ቆሻሻ ኬሚካል በሚወጣ ጭስ የተነሳ በዓመት 58 ሺህ 975 ኢራናውያን መሞታቸው ተገለጸ፡፡
ኢራን የገጠማትን የኃይል እጥረት ለመወጣት በምታደርገው ጥረት የሀገሪቱ ባለስልጣናት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ሰልፈርና ሌሎች አደገኛ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ከፔትሮሊየም ቅሪት የሚገኝ ማዙት የሚባል ቆሻሻ ኬሚካል ሲያቃጥሉ መቆየታቸው ተገልጿል።
እንደቀዳሚዎቹ የኢራን መሪዎች ሁሉ የፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዢኪሃን መንግሥትም ሀገሪቱ የገጠማትን የኃይል እጥረት ለመፍታት ይህንን ማዙት የሚባል አደገኛ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ቆሻሻ ከሚካል ማቃጠልን በአማራጭነት መጠቀም መቀጠሉን አልጀዚራ ዘግቧል።
በዚህም በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 14 የሚደርሱ የማዙት ቆሻሻ ኬሚካል ማቃጠያ ጣቢያዎች እስከ ሕዳር አጋማሽ ድረስ በየቀኑ 21 ሚሊዮን ሊትር ወይንም 5 ነጥብ 55 ሚሊዮን ጋሎን የማዙት ቆሻሻ ኬሚካል እየተቃጠለ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ሲውል መቆየቱን ለኢራን ኢስላማዊ አብዮት ጥበቃ ኃይል ቅርበት ካለው ፋርስ ኒውስ ኤጀንሲ የተገኙ የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
ከማቃጠያ ጣቢያዎቹ የሚወጣው አደገኛ ጭስ በሚፈጠረው የአየር ብክለት የተነሳም በኢራናውያን የቀን አቆጣጠር እስካለፈው መጋቢት ድረስ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 58 ሺህ 975 ኢራናውያን መሞታቸውን የኢራን ምክትል የጤና ሚኒስትር አሊሬዛ ሬይሲ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። በሌላ አገላለጽ ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ በየቀኑ 161 ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ ማለት ነው።



