የማሌዥያ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት “ከተለመደው ዲፕሎማሲ ያለፈ ነው” አሉ የማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር::

ኢትዮ ሞኒተር፡ 11/03/2018፡- የማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት “እጅግ ትርጉም ያለውና ፍሬያማ” ሲሉ የገለፁት ሲሆኑ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነትም “ከተለመደው ዲፕሎማሲ በላይ” መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የማሌዥያው ጠቅላይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር በብሄራዊ ቤተመንግስት ውይይት በደረጉበት ወቅት ዳቶ ሰሪ “የማሌዥያ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከተለመደው ዲፕሎማሲ በላይ እንደሆነ ነግሬያቸዋለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተዘጋጀው የእራት ግብዣ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ “በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጠበቀ ወዳጅነት፣ የጋራ እድገትና ሁለንተናዊ የሰብአዊ እሴቶች ላይ የተመሰረተውን ትስስር ለማጠናከር መስራቴን እቀጥላለሁ” ብለዋል።
ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም በጋዛ ውስጥ ያለውን ስቃይ እና በሱዳን ውስጥ ያለውን ግጭት ጨምሮ በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ በሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ መወያየታቸው ተገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን ጎብኝተዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ ጉብኝቱ የማሌዢያ እና የአፍሪካን ግንኙነት የሚያጠናክር ታሪካዊ ጉብኝት መሆኑን ተናግረዋል።



