“ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮች ሲፈጽሙ” ተገኘኙ የተባሉ 112 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለፀ

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/03/2018፡- “ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ የተደረሰባቸው” 112 ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል የፀጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ ጥቆማ በተደረገ የተቀናጀ ሥምሪት “በፋይናንስ አሻጥር የተሰማሩ” 112 ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም “ከሕገ ወጥ ተግባሩ ጋር ትስስር የነበራቸው” 519 የባንክ አካውንቶች መታገዳቸው የተገለፀ ሲሆን የተለያዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውም ተጠቁሟል፡፡
“በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ላይ በማነጣጠር ሲፈጸም የነበረው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማስተጓጎል፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ በተቀናጀ መንገድ ሲፈጽሙት እንደነበረ” መግለጫው አመልክቷል፡፡
መግለጫው በተጨማሪም “ሕገ ወጥ ሃዋላዎች ፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራዎች ፣ የግብር ስወራዎች፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰልና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችንና የታጠቁ ቡድኖችን ለመደገፍ ሲውሉ መቆየታቸውን” ገልጿል፡፡
በተለይም ሕገ ወጥ በሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፣ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፣ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፣ ሕገ ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች፣ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈፀሙ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ አካላት ላይ የማያዳግም ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱ ነው የተገለፀው፡፡
“በሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሀብትን ከሀገር በማሸሽ ላይ ያሉ ድርጅቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል” ያለው መግለጫው አያይዞም “የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካለት ላይም ርምጃ ተወስዷል” ብሏል፡፡
“አገልግሎቱ የሀገርን ደኅንነት ስጋት ላይ በሚጥሉ እና የሀገርን ኢኮኖሚ በሚጎዱ አሻጥሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በመከታተል የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል” ገልጾ “መላው ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰል ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል” ጥሪ አቅርቧል፡፡
በቅርቡ “በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተዋል” የተባሉ የ123 ተጠሪጣሪዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ መደረጉን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ማስታወቁን ይታወሳል፡፡



