ዲፕሎማሲ
ግብፅ በጅቡቲ አዲስ ወደብ እና የሎጂስቲክስ ማዕከላትን ልትገነባ ነው ተባለ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/03/2018፡- ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ንግድ መተላለፊያ በሆነችው ጅቡቲ ውስጥ ግብፅ ትልቅ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ልታደርግ መሆኑን አስታውቃለች።
ይህም ግብፅ አዲስ የወደብ እና የሎጂስቲክስ መገልገያዎችን ለመገንባት በሚያስችላት የትብብር ስምምነት ላይ ለመድረስዋ ነው የተገለፀው።
በግብፅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ ጅቡቲ በሚያደርገው ይፋዊ ጉብኝት ወቅት ስምምነቱ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የትብብሩ መሠረት የተጣለው በኅዳር 3 ቀን 2025 ዓ.ም በግብፅ ልዑካን እና በጅቡቲ ወደቦች እና ነፃ ቀጠና ባለስልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኦማር ሃዲ መካከል በተደረገ ስብሰባ ነው።
በዚህ የኢንዱስትሪ ልማት ላይ የግብጽ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ካመል ኤል-ዋዚር በቅርቡ የሚያደርጉት ጉብኝት ለስምምነቱ የመጨረሻ ፊርማ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ይህ ሰፊ ፕሮጀክት ጅቡቲ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን የንግድ ማዕከልነት ሚና ከፍ የሚያደርጉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ያካትታል ተብሏል።
በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ያልተሳካለት ግብፅ ባልታሰበ አቅጣጫ ብቅ ብላለች፡፡
ኣንዴ በሶማሊያ፣ ሌላ ግዜ በኤርትራ አሁን ደግሞ በጅቡቲ ኢትዮጵያን የመክበብና በዲፕሎማሲ የመነጠል ስራ እየሰራች እንደሆነ ይገለፃል፡፡



