” ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልጽ አፍርሷል ” ሲል የአፋር ክልል መንግስት ከሰሰ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/02/2018፡-“የህወሓት ቡድን በዛሬው ዕለት በአፋር ክልል ወሰን ውስጥ በማግባት 6 መንደሮችን በጉልበት በመቆጣጠር ንጹሃንን በሞርታርና በዙ-23 ደብድቧል ” ሲል የአፋር ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ አስታውቀዋል።
” በዛሬው ዕለት ማለትም ጥቅምት 26 ቀን 2018 ዓ/ም የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል በዞን ሁለት በመጋሌ ወረዳ ቶንሳ ቀበሌ ዋራዓ እና ሚልኪ በሚባሉ ልዩ አካባቢዎች ወሰን ተሻግሮ በመግባት ከምሽቱ አንድ ሰአት አካባቢ በንጹሐን የአፋር አርብቶ-አደሮች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በመክፈት የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግጭት አዋጅ በግልጽ አፍርሷል ” ሲልም አሳውቋል።
“ይህ የህወሓት ጣብ-ጫሪ ቡድን በቶንሳ ቀበሌ ላይ ተኩስ በሚከፈትበት ወቅት ሰላም ወዳድ የአፋር ሽማግሌዎች እንድመለሱ ቢማፀኗቸውም የህወሓት ቡድን ግን አሻፈረኝ በማለት ግጭቱን አስከትሏል ” ብሏል።
” ይህ ከትናንት ጥፋቱ የማይማረው ተስፋ ቢሱ የህወሓት ቡድን ከድርጊቱ በአስቸኳይ ካልተቆጠበ የዜጎች ደህንነትና የወሰናችንን ክብር የማስጠበቅ፣ እንዲሁም ራሳችንን ከማንኛውም ውጫዊ ጥቃት የመከላከል ኃላፊነታችን እንደምንወጣ እንገልፃለን ” ሲል የአፋር ክልል መንግሥት አስጠንቅቋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ጌታቸው ረዳ ትናንት በአፋር ክልል ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት “ የሻዕቢያ ትዕዛዝ ነው፤ አስፈጻሚዎቹም ፍሰሃ ማንጁስና ዮሐንስ መዲድ ናቸው “ ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ጌታቸው ማሳሰቢያ ለልባሞች፣ ሲሉ ሰይመው በፌስቡክ አድራሻቸው በለጠፉት ጽሁፍ ኋላ ቀሩ አያሉ የጠሩት ቡድን “ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ቀዶ ለመጣል ሁሉም ዓይነት ትንኮሳ ቢሞክርም፣ የፌደራል መንግስት ግብረ መልስ ሳይሰጣቸው ዝም በማለቱ፣ አሁን የፌደራል መንግስትን ጎትተው ወደ ግጨት ለማስገባት በማለም በአፋር ትንኮሳ እየፈጸሙ ነው “ ሲሉ ከስዋል፡፡
ይህ ትንኮሳ አለቃቸው ሲሉ የጠሩት ሻዕቢያ ትዕዛዝ አጀንዳ ነው ያሉት ጌታቸው “ ለዚህም ቀዳሚ ተጠያቂዎቹ ፍሰሃ ማንጁና ዮሐንስ መዲድ ናቸው “ ብለዋል፡፡
በአፋሩ መንግስት ክስ ዙሪያ ህወሓት ይሁን የትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር ያሉት ነገር የለም፡፡
ሰሙኑን በአፋር ሓራ መሬት እያለ በሚጠራው የሚገኝ የትግራይ ታጣቂ ቡድን ወደ ትግራይ ዘልቆ ትንኮሳ መፈጸሙና ከክልሉ የፀጥታ ሐይል ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡



