ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢንዱስትሪ፣ በኃይልና በመሠረተ ልማት ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ውይይት ማድረጋቸው ተሰማ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/02/2018፡- ኢትዮጵያና ሩሲያ በኢንዱስትሪ፣ በኃይል እና በመሠረተ ልማት እንዲሁም በሌሎች በዋና ዋና ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ያለመ ከፍተኛ ውይይት ማካሄዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቅዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሥራ አስፈፃሚ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ማክሲም ኦሬሽኪ እና ከሩሲያ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ማክሲም ሬሼትኒኮቭን ጋር ተገናኝተው በስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዎን በሁለቱ አገሮች መካከል ረዥም ዓመት ያስቆጠረ ግንኙነት መኖሩን በመጥቀስ፤ ሩሲያ በተለያዩ የትብብር መስኮች ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትሩ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ (ICT) እና በማዕድን ልማት ኢንቨስትመንት እንዲሁም በማዳበሪያ ምርት፣ በብረታ ብረት እና በኑክሌር እና ታዳሽ የኃይል ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የኃይል መሠረተ ልማት ዘረፎች ለሩሲያ የኢንቨስትመንት እና የጋራ ሥራዎች ጥሪ አቅርበዋል።
የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ እንደዘገበው፣ የሩሲያ ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ማክሲም ሬሼትኒኮቭን፣ ሩሲያ ከኤትዮጵያ ጋር በኢንዱስትሪ፣ በኃይል፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ትብብሯን ለማስፋት ዕድሎችን እንደምታይ ገልጸዋል።



