የሱዳን ትይዩ መንግስት አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 24/02/2018፡- በሌተና ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራውና ራሱን ‹‹ሱዳን ፋውንዲንግ አሊያንስ›› ብሎ የሚጠራው ትይዩ መንግስት በአስቸኳይ ተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዚህ ትይዩ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት መሀመድ ሀሰን አል ታይሺ ባደረጉት ንግግር የጦር ሀይላቸው በቅርቡ ወታደራዊ ድል መቀዳጀቱን ገልፀው ‹‹አሁን ዳርፉር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ስር ይገኛል›› ብለዋል፡፡
አልፋሽርና ባራ አካባቢዎች ወደአዲስ ምእራፍ ውስጥ መሸጋገራቸውን የጠቀሱት የቤ,ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግስት መዋቅር ዝርጋታ እየተከናወነባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በትይዩ መንግስቱ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ህዝቦች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበውም ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንደሚያሰፍኑ ቃል ገብተዋል፡፡
ለደረሰው የመብት ጥሰትና ህገ ወጥ ግድያ አስቸኳይና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ግጭትን ለማስቆም በሚደረግ ማንኛውም ውይይትና ንግግር ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹አሁን በአስቸኳይ ተኩስ አቁም መደረግ ይኖርበታል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ከዚህ ቀደም ከተጀመሩና ወደፊትም በሚጀመሩ የድርድር ጠረንጴዛዎች ላይ ለመቀመጥ ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሳኡዲ አረቢያና ዩናይትድ አረብ ኤመሬትስ አማካኝነት በተጀመረው የአራትዮሽ የሰላም ጥረት ላይ ጭምር ለመተባበር መንግስታቸው ፈቃደኛ መሆኑንም አስረድተዋል ሲል ሱዳን ታይምስ ዘግቧል፡፡



