ፖለቲካ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ በመጪው ግንቦት 24፤ 2018 ለማድረግ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ተሰማ።
ቦርዱ በምርጫው የሚገኘውን ውጤት ይፋ ለማድረግ፤ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ያስቀመጠው ዕለት ሰኔ 3 ነው።

ኢትዮ ሞኒር፡ 13/02/2018፡- ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫውን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ ለውይይት ያቀረበው፤ ጥቅምት 10 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር ሲሆን ከ60 በላይ በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች መሳተፋቸውን ተገልፀዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ባልተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፤ ምርጫ ቦርድ የ7ተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳ ማቅረቡን ተሰምተዋል፡፡
በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው፤ ከህዳር መጀመሪያ እስከ ወሩ አጋማሽ ድረስ በምርጫ ለሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች የምዝገባ ጥሪ ለማድረግ ታቅዷል።
የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለህዝብ ይፋ ማድረግ፤ ህዳር 19 ተጀምሮ በጥር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ለማጠናቀቅ የታሰበ ሲሆን ይህ መርሃ ግብር በሁለት ዙር የሚከናወን መሆኑ በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተመልክቷል።
በምርጫ የሚሳተፉ ዕጩዎች ምዝገባ እንዲከናወን የታቀደው ከታህሳስ መጀመሪያ እስከ ጥር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የምረጡኝ ቅስቀሳ ከታህሳስ 10 እስከ ግንቦት 19 ድረስ እንዲከናወን ቦርዱ አቅዷል።