የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይል በኤል ፋሸር በሲቪሎች ላይ ለሚያደርሰው ጥቃት ተጠያቂነት ጠየቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 03/02/2018፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤል ፋሸር፣ ሰሜን ዳርፉር በፈጣን ድጋፍ ሃይሎች ተፈፅሟል የተባለውን “ተደጋጋሚ እና ሆን ተብሎ” በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት አጥብቆ አውግዟል፤ ጥፋተኞችም በህግ እንዲጠየቁ ጠይቋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) እሁድ በለቀቀው መግለጫ በቅርቡ የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ እና የከተማዋ ሆስፒታል ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ጨምሮ በትንሹ 110 ንፁሀን ዜጎችን የገደሉ ጥቃቶችን ዘርዝሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥቃቱን በማውገዝ “እነዚህ ክስተቶች ጥልቅ የሆነ ገለልተኛ ምርመራ ይፈልጋሉ እና ተጠያቂዎችም ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ብሏል።
ውግዘቱ የተሰማው በጥቅምት 10 እና 11 በዳራጃ ኦላ ሰፈር ውስጥ በተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ላይ በተፈፀመ ከባድ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃቶች ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 57 ንፁሀን ዜጎችን ከተገደሉ በኃላ ነው።
ቀደም ብሎ፣ በጥቅምት 5 እና 8 መካከል፣ በታጣቂ ሐይሉ የተመዘገቢ ተከታታይ ጥቃቶች በትንሹ 53 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ከ60 በላይ ቆስለዋል ብሏል ድርጅቱ።
ቁልፍ ኢላማ ያደረገው የሳዑዲ ሆስፒታል ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት “በከተማው ውስጥ በታሰሩ ሲቪሎች ህልውና ላይም ከባድ ጉዳት አድርሷል” ሲል ገለፀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቆ በግጭቱ የተጎዱትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።