የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የሱዳንን መርማሪ ቡድን ቆይታ ለአንድ አመት አራዘመ።
የቀረበው የሁለት ዓመት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/01/2018፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳን ያለውን የምርመራ ተልዕኮ ለአንድ አመት እንዲራዘም ድምጽ ሰጥቷል።
የገለልተኛ አለም አቀፍ እውነታ ፍለጋ ተልዕኮን የስልጣን ጊዜ ለማራዘም የተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ በ24 ድጋፍ እና በ11 ተቃውሞ በ12 ድምጸ ተአቅቦ ጸድቋል።
የሱዳን ጦር እና የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይሎች የጦር ወንጀሎች የሚያደርሱ ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የሚያረጋግጠው ቡድን በመስከረም ወር ያወጣውን አስከፊ ሪፖርት ተከትሎ ነው ቆይታው እንዲራዘም የተደረገው።
መርማሪ ቡድኑ ድጋፍ ሰጪ ሐይሉ በሰብአዊነት ላይ ወንጀል እንደፈፀመ የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ማግኘቱ ተገልጿል።
“በሁሉም አካላት የተፈጸሙ ወንጀሎችን በመመዝገብ እና በማጋለጥ እውነታ አፈላላጊው ቡድን ተጠያቂነትን በማስፈን ለሱዳን ግጭት የረዥም ጊዜ መፍትሄ ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል ያግዛል” ሲሉ የመብት ተሟጋቾች ቡድን ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሽሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቋል።
የውሳኔ ሃሳቡ ግድያን፣ ማሰቃየትን፣ አስገድዶ መድፈርን፣ በሲቪል አከባቢዎች ላይ የሚደርሰውን ድብደባ እና ረሃብን እንደጦር መሳሪያ መጠቀምን ጨምሮ ሰፊ ጥሰቶችን ግምት ውስጥ አስገብቷል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በጎሳ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ቀደም ሲል በዳርፉር ከተፈጸሙ ግፎች “ መመሳሰል” እንዳላቸው አስጠንቅቋል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እድሳቱን በደስታ ቢቀበሉም፣ ያነሱት የሁለት አመት ማራዘሚያ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘቱ ተልዕኮው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቀጥተኛ ምክሮችን እንዲያቀርብ የሚያስችል ድንጋጌ አላካተተም ብለዋል።