አፍሪካ
ዓለማቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት አይ ሲ ሲ በሱዳን ዳርፉር የጦር እና በሰብአዊነት ላይ ለተፈጸመ ወንጀል የተተከሰሱትን የሚሊሻ መሪ አሊ ሙሐመድ አሊ አብዱልራህማን የጥፋተኝነት ብይን ሰጠ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/01/2018፡- ኖም ዲ ጉኤሬ አሊ ኩሻይብ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት አብዱልራህማን በአ.አ.አ ከ2003 እስከ 2004 ግድያ እና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በ31 የወንጀል ክሶች ነበር የተከሰሱት።
የዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ዓቃቢያነ ህግ እንዳሉት የጃንጃዊድ ሚሊሻ ግንባር ቀደም አባል የነበሩት አብዱራህማን በበርካታ የጦር ወንጀሎች የጎላ ተሳትፎ ነበራቸው።
የ75 ዓመቱ ተከሳሽ ግን ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃላቸው የቀረበባቸውን ሁሉንም ክስ አስተባብለዋል።
ፍርድ ቤቱ የተሳሳተ ሰው ለፍርድ ማቅረቡንም ነው የገለጡት ።
በ2020 በሱዳን የተመሰረተው አዲስ መንግስት ከዓለማቀፉ የወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኑን ተከትሎ አብዱልራህማን ወደ ጎረቤት ሀገር ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተሰደው ነበር ።
ባለስልጣናት “ግድያ ሊፈጽሙብኝ ነው” የሚል ስጋት አድሮባቸው እንደነበረ የገለጹት ተከሳሹ ይኸው ስጋት ራሳቸውን ለዓለማቀፉ ፍርድ ቤት አሳልፈው ለመስጠት እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ2000ዎቹ የዳርፉር ግጭት 300 ሺ ያህል ሰዎች ሲገደሉ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።