የተለያዩ
የቀድሞው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ በሌሉበት በጦር ወንጀሎች እና አገር መክዳት ወንጀሎች ሞት ተፈረደባቸው።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 21/01/2018፡- ካቢላ ላይ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክልል ከፍተኛ ውድመት ያደረሱትን ኤም23 አማፂያን ይደግፋሉ የሚል ይገኝበታል።
አርብ ዕለት የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በአገር ክህደት፣በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል፣ እንዲሁም ግድያ፣ የወሲብ ጥቃት፣ ማሰቃየት እና ማመጽን ጨምሮ በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጥፋተኛ ናቸው ብሏል።
ካቢላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ቢናገሩም ችሎት ፊት ቀርበው ግን ራሳቸውን አልተከላከሉም።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክሱን “በዘፈቀደ” የጠመሰረተ ያሉ ሲሆን ችሎቱን ደግሞ “ለጭቆና መሣሪያ ሆኗል” በማለት ውድቅ አድርገውታል።
ጆሴፍ ካቢላ አሁን የት እንዳሉ አይታወቅም።
የ54 ዓመቱ ካቢላ እአአ በ2001 በጥይት የተገደሉትን አባታቸው ላውረንት በመተካት ለ18 ዓመታት አገሪቱን አስተዳድረዋል።
ካቢላ እአአ በ2019 ለፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ያስረከቡ ቢሆንም በኋላ ግን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት እአአ በ2023 በፈቃዳቸው አገሪቱን ለቅቀው ተሰድደዋል።