“የኢትዮጵያ መንግስት ግዴታዎቹን ማክበር አልቻለም” ሲል ህወሐት ከሰሰ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 20/01/2018፡- ህወሐት ትላንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ባለፈው ሳምንት በመቐለ ተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ በጅብ በተገደለውን ጨቅላ ህፃን ማዘኑን ገልጿል፡፡
“የአንድ አመት ከአራት ወር እድሜ ያለው ናኦድ ሀይለስላሴ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ክስተት ከምእራብ ትግራይ የተፈናቀሉ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ የሚደርስባቸውን ስቃይ የሚያሳይ ነው” ያለው ህወሐት እነዚህ ተፈናቃዮች በምግብ፣ መድሀኒት፣ መጠለያና ክብር እጦት እየተሰቃዩ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡
“ከዛሬ 3 አመት በፊት የተፈረመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ሰላም እንደሚሰፍን፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቤታቸው እንደሚመለሱና ወራሪ ሀይሎች ለቀው እንደሚወጡ ቃል የተገባበት ነበር ያለው ህወሓት ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ግዴታዎቹን ማክበር አልቻለም” ሲል ከሷል።
በስምምነቱ ላይ የሰፈሩት አብዛኛዎቹ ድንጋጌዎች አለመፈፀማቸውም ጠቅሷል፡፡
ላለፉት አምስት አመታት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በረሀብ፣ በበሽታና በተጋላጭነት ለችግር መጋለጣቸውን የጠቀሰው መግለጫው ይህ የሆነው ደግሞ “በእድል ሳይሆን በሰላም ሽፋን በሚደረግ ስልታዊ ቸልተኝነት ነው” ብሏል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን በተለይም ወራሪ ሀይሎ በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ፣ በወረራ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ስቃይ እንዲያበቃና ተፈናቃዮች በሰላም ወደነበሩበት ቤታቸው እንዲመለሱ ህወሓት ጠይቋል ፡፡
በፕሪቶሪያው ስምምነት ወቅት ዋስትና ለሰጡት አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተደጋጋሚ በዚህ ጉዳይ ላይ አቤቱታ ቢቀርብላቸውም ዝምታን መምረጣቸውን የጠቀሰው ህወሓት አለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡