
ኢትዮ ሞኒተር፡ 20/01/2018፡- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አዲስ የጋዛ የሰላም ዕቅድን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቋል።
የሁለቱ መሪዎች ዕቅድ፤ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በአፋጣኝ እንዲቆሙ እንዲሁም ሐማስ በ72 ሰዓታት ውስጥ 20 እስራኤላውያን ታጋቾችን እና የሞቱ ታጋቾችን አስክሬን እንዲያስረክብ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።
በምላሹም በመቶዎች የሚቆጠሩ የታገቱ የጋዛ ነዋሪዎች ይለቀቃሉ ተብሏል።
መሪዎቹ በዋይት ሀውስ ውይይት ካደረጉ በኋላ በሰጡት መግለጫ ትራምፕ “ለሰላም ታሪካዊ ቀን” ሲሉ ዕቅዱን አሞካሽተዋል።
ሐማስ በሰላም ዕቅዱ የማይስማማ ከሆነ ኔታንያሁ “የጀመሩትን ሐማስን የማጥፋት ዘመቻ” አሜሪካ እንደምትደግፍም አክለዋል።
ኔታንያሁም ሐማስ ዕቅዱን ካልተቀበለ ወይም ካልተገበረ እስራኤል “የጀመረችውን ትጨርሳለች” ሲሉ ዝተዋል።
በእስራኤል ይዞታ ሥር የሚገኘውን ዌስት ባንክ የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አመራር ትራምፕ እያደረጉ ያሉት ጥረት “ቆራጥነት የተሞላው እና እውነተኛ ነው” ብሏል።
የፍልስጤሙ ዋፋ የዜና ኤጀንሲ ላይ በወጣው መግለጫ የፍልስጤም አስተዳደር “በጋዛ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለማስቆም ከአሜሪካ፣ ከቀጣናው አገራትና አጋሮቻችን ጋር በጋራ ለመሥራት አሁንም ቁርጠኛ ነን” ሲል አቋሙን አስታውቋል።
አስተዳደሩ፤ ጦርነቱን ከማስቆም በተጨማሪ ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ እንዲሁም የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ እንዲካሄድ እንደሚሠራ ገልጿል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ካታር፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዥያ እና ፓኪስታን በጋራ ባወጡት መግለጫ “ትራምፕ የጋዛን ጦርነት ለመግታት እያደረጉ ያሉትን ያላሰለሰ ጥረት እንደግፋለን” ብለዋል።
ስምምነቱ እንዲተገበር ከአሜሪካ ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውንም አክለዋል።
የሰላም ዕቅዱ የሁለት አገራት መፍትሔ መስጠት እንዳለበት እና ጋዛ ከዌስት ባንክ ጋር ተሳስራ የጠቅላላው የፍልስጤም አስተዳደር አካል መሆን እንዳለባት አገራቱ ገልጸዋል።
ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ቅርብ የሆኑ የፍልስጤም ምንጭ ለቢቢሲ አንደተናገሩት፣ ዋይት ሀውስ ለሐማስ 20 ነጥቦችን አቅርቧል።
ሐማስ ጋዛን ከዚህ በኋላ ማስተዳደር እንደማይችል እና ፍልስጤም እንደ አገር እንድትመሠረት እንደማይፈቅዱም ኔታኒያሁ ተጠቅሷል።
የቀረበው የሰላም ዕቅድ የሚተገበር ከሆነ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በአፋጣኝ የሚገቱ ይሆናል።
አሁን ያሉ “የጦር ግንባሮች” ባሉበት እንደሚቆዩና ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ ወታደሮች ለቀው እንደሚወጡ ይጠበቃል።
ትራምፕ ባወጡት ዕቅድ መሠረት፣ ሐማስ ጦሩን ፈትቶ የመሣሪያ ማምረቻ ተቋማቱ ይወድማሉ።
የአንድ እስራኤላዊ ታጋች አስክሬን ሲለቀቅ እስራኤል የ15 የጋዛ ነዋሪዎችን አስክሬን በምላሹ ታስረክባለች።
ሁለቱም ወገኖች በሰላም ዕቅዱ የሚስማሙ ከሆነ ወደ ጋዛ “ሙሉ ሰብአዊ እርዳታ” እንደሚገባም ተገልጿል።
አሜሪካ በቀጣይ ጋዛን ማን ያስተዳድራል በሚለው ላይ የወጠነችውን ዕቅድ አስቀምጣለች።
ጋዛን በጊዜያዊነት “ከፖለቲካ ነጻ የሆነ ኮሚቴ” እንደሚመራት እንዲሁም “አዲስ ዓለም አቀፍ የሽግግር ጊዜ ተቆጣጣሪ አካል” አስተዳደሩን እንደሚከታተል ተገልጿል።
ይህንን ተቆጣጣሪ አካል የሚሾሙት ትራምፕ ይሆናሉ።
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር የዚህ ተቆጣጣሪ አካል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።