ኢኮኖሚ

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የንግድ ሥራን “የማይቻል” እያደረገው መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት ይፋ አደረገ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 20/01/2018፡- በአዲስ አበባ ተጀምሮ ቢያንስ በ40 የአገሪቱ ከተሞች በመካሄድ ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የንግድ ሥራን “የማይቻል” እያደረገው መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ሪፖርት ገለጸ።

የአሜሪካ ኩባንያዎች በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ በሚል በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በያመቱ የሚዘጋጀው ይህ ሪፖርት፤ ከ170 በላይ የሚሆኑ አገራትን የኢንቨስትመንት አመቺነት ሁኔታ የሚዳስስ ሲሆን አርብ መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው የዘንድሮው ሪፖርቱ የኢትዮጵያን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የንግድ ሥራን “የማይቻል” እያደረገው ነው ብሏል።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶቹ ከንግድ ቦታዎች ፊት ለፊት ያሉ መንገዶችን በማፍረስ የሚከናወኑ መሆናቸውን የጠቆመው የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት፤ ይህም የንግድ ሥራን “የማይቻል” እያደረገው መምጣቱን ያትታል።

“በዚህም የንግድ ሥራዎች ቀጥታ ባይነኩም እንኳ ከሥራ እንዲወጡ እየተገደዱ ነው” ብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም አንዳንድ የውጭ እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ድንገተኛ እና ከፍተኛ የግብር ግመታ ወይም ወደ ኋላ ተመልሶ በሚሰራ አዲስ ሕግ የተነሳ የመጣ የግብር ጥያቄ እያጋጠማቸው መሆኑን መግለጻቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።

የግብር ጥያቄዎች እየቀረቡት ያሉት በቂ ግልጽነት ወይም አሰራርን ሳይከተሉ እንደሆነ የሚያትተው ሪፖርቱ፤ ይህም ትርፋቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ያደረገና እርምጃው ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የባለቤትነት መብት ማሳጣት ድርጊትን የሚያበረታታ መሆኑንም ጠቅሷል።

በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶቹ የተነሳ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና ንግዶች መባረራቸውንና ንብረቶቻቸውም በትንሽ እና ያለምንም ማስጠንቀቂያ ወይም ካሳ መፍረሱን ያስታወሰው የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት፤ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶቹ የተነሳ የሚፈጸሙ መፈናቀሎች፣ የንግድ ቦታ ፈረሳዎች፣ ከፕሮጀክቶቹ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ሙስናዎች የንብረት ጥሰት ማስከተላቸውንና ይህም የባለሀብቶችን መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እየገደበው መሆኑን አመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም “በሀገሪቱ ውስጥ በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ያሉ ግጭቶች እንዲሁም እንደገና እየሰፋ የመጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ልዩነት የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለአሜሪካ እና ሌሎች የውጭ ንግዶች ፈታኝ አድርጎታል” ብሏል ዓመታዊ የአሜሪካ መንግሥት የኢንቨስትመንት ሁኔታ ሪፖርት።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates