
ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/01/2018፡- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ልዩ መልእከተኛ ማሳድ ቦሎስ ከኤርትራ ባለስልጣናት ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል።
አፍሪካ ኢንተሌጅንስ እንደዘገበው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማሳድ ቦሎስ ከኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ሊገናኙ ነው።
ዋሽንግተን በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ግጭቶች መስፋፋት እንዳሳሰባት የጠቆመው መረጃው ማሳድ ቦሎስ ከኤርትራው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዑስማን ሳሊህ ጋር ተገናኝቶ እንደሚነጋገሩ ዘገባው አመልክቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ልዩ መልእክተኛ ቦሎስ ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም በቀጠናው ፀጥታና ደህንነት መወያየታቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር በር ጥያቄዋ በውይይት እና ድርድር እንድታስኬደው ቦሎስ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
አሁን ደግሞ አሜሪካ ለኤርትራ ባለስልጣናት ተመሳሳይ መልእክት ለማስተላለፍ ማቀዷ ተሰምቷል።
የኤርትራ ባለስልጣናት ለኤትዮጵያ ባለስልጣናት ተከታታይ በሚባል መልኩ መልስ እየሰጡ ይገኛሉ።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል በተከታታይ ኢትዮጵያን እየከሰሱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያን ገዥ ፓርቲ ብልፅግናን “የይስሙላ ፓርቲ” ሲሉ በመኮነን፣ የፓርቲው የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለስልጣናት “የሉዓላዊ የባህር በር የማግኘት” ፍላጎታቸውን “ቅዠት” እና “አደገኛ አካሄድ” ሲሉ በጠንካራ ቃላት አውግዘዋል።
ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ተከታታይ መልዕክት፣ የብልፅግና ፓርቲ ባለስልጣናት ይህንን አጀንዳ “የተለመደ” ለማስመሰል ከፍተኛ ዘመቻ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ የማነ የብልፅግና ፓርቲ አካሄድ ከዚህም አልፎ በሁለቱ ሀገራት ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ “ጨለማ ምዕራፍ” የነበረውን የኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ የመጠቃለል ዘመንን በማጣቀስ እና በማወደስ ላይ መሆናቸውን ከሰዋል። ይህ ድርጊት “ህገ-ወጥ እና አጸያፊ” ከመሆኑም በላይ “ሊታሰብበት ወይም ሊታለፍ የማይገባው ቀይ መስመር” እና “የፖለቲካ ክህደት” ነው ሲሉ አክለዋል።
ይህ ከግዜ ወደ ግዜ እየሻከረ እየመጣ ያለውን የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ወደ ጦርነት አምርቶ የቀጠናው ጦስ እንዳይሆን የአሜሪካ ስጋት ነው።
ለዚህም ነው አሜሪካ ጉዳዩ በውይይት እንዳፈታ ጥረት እያደረገች የምትገኘው።