“በ7 ወራት ውስጥ 7 ማብቂያ የሌላቸውን ጦርነቶች አስቁሜያለሁ” ሲሉ ትራምፕ ተናገሩ፡፡
በዩክሬንና ሩስያ የአቋም ለውጥ የተባለለት አወዛጋቢ አስተያየት ሰጥቷል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 14/01/2018፡- የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል የነበረውን ግጭት እንደፈቱት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን ይህንን አሁንም በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ደግመውታል፡፡
ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው “በ7 ወራት ውስጥ 7 ማብቂያ የሌላቸውን ጦርነቶች አስቁሜያለሁ” ካሉ በኋላ ያስቆሟቸው ጦርነቶች አንዳንዶቹ 31 አመታትን የፈጁና አንደኛው ደግሞ 36 የሞላው እንደነበር ገልፀዋል።
እነዚህ ጦርነቶችም የኢትዮጵያና ግብፅ፣ የካምቦዲያና ታይላንድ፣ የሰርቢያ ኮሶቮ፣ የኮንጎና ሩዋንዳ፣ የፓኪስታንና ህንድ፣ የእስራኤልና ኢራን እንዲሁም የአርሜኒያና የአዘርባጃን መሆናቸውን ዝርዝረው “በእነዚህ ጦርነቶች ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ሲገደሉ ነበር” ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ስያደርጉ ተመድ አንድም ቀን እንኳን ጥረታቸው ለማድነቅና ለመደገፍ ስልክ ጀውሎላቸው እንደማያውቅ በመጥቀስ ድርጅቱን ችግርን አባባሽ ብሎታል።
ይህ እንዲህ እያለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዩክሬንና ሩስያ የአቋም ለውጥ የተባለለት አወዛጋቢ አስተያየት ሰጥቷል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን በአውሮፓ ህብረት እና በኔቶ ድጋፍ ሩሲያ ከሶስት አመታት በፊት የወረረችባትን ግዛት በሙሉ መልሳ ማግኘት እንደምትችል አምናለሁ ሲሉ ተናግሯል።
“በጊዜ፣ በትዕግስት እና በአውሮፓ የገንዘብ ድጋፍ በተለይም በኔቶ እርዳታ ይህ ጦርነት በተጀመረበት ወቅት ወደ ነበረው የዩክሬን ድንበር መመለስ አማራጭ ነው” ሲሉ ትራምፕ ማክሰኞ እለት ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር ከተገናኙ በኋላ በግል ንብረታቸው በሆነው ትሩዝ ማህበራዊ መድረክ ላይ አጋርተዋል።
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን መሪዎቹ ተገናኝተው መክረዋል።
ጦርነቱን ለማቆም ሁለቱም ኪየቭ እና ሞስኮ መሬት መስጠት አለባቸው ሲሉ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
ዜለንስኪ እና የአውሮፓ አጋሮቹ ሰላምን ለማግኘት የትራምፕን የግዛት ስምምነት ሃሳብ መቃወማቸው ይታወሳል።
ትራምፕ የሩሲያን የግጭት ክስ በመቃወም “ያለ አላማ” በጦርነት ውስጥ መቆየቷን እና “እውነተኛ ወታደራዊ ኃይል” በ “ሳምንት ባነሰ ጊዜ” ውስጥ ያሸንፋል በማለት ተችተዋል።
ትራምፕ እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ሩሲያ ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ናቸው እናም ዩክሬን እርምጃ የምትወስድበት ጊዜው አሁን ነው ሲሉ አክለዋል።
ሩሲያ “የወረቀት ነብር” ሲሉ አጣጥለዋታል ።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 ወረራ ከፈፀመች በኋላ 20 በመቶ የሚጠጋውን የዩክሬን ግዛት በቁጥጥር ስር አውላለች።
ትራምፕ “ዩክሬን ለምታደርገው ትግል ትልቅ ክብር እንዳላቸው በማንሳት በእውነቱ በጣም አስደናቂ ነው ። ” ሲሉ ተደምጠዋል።