
ኢትዮ ሞኒተር፡ 06/01/2018፡- ኤምባሲው በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ያወጣውን “የጉዞ ማስጠንቀቂያዎች ወሳኝ ናቸው” በማለት ዜጎቹ የስቴት ዲፓርትመንትን የጉዞ ማሳሰቢያዎች በጥብቅ እንዲከተሉ አሳስቧል።
የኤምባሲው መልዕክት ከዚህ ቀደም ከሚሰጡት አጠቃላይ የጸጥታ ማስጠንቀቂያዎች የተለየ ሲሆን በተለይ “በመንግስታት የሚፈጸም በግፍ የመታሰር” አስፈጻሚ ትዕዛዝን መጥቀሱ፣ ስጋቱ ከተራ ወንጀል ወይም ከሲቪል አለመረጋጋት የዘለለ መሆኑን ብዙዎች እየገለፁ ይገኛሉ።
ይህ የስቴት ዲፓርትመንት አስፈጻሚ ትዕዛዝ፣ የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹን ያለ በቂ ህጋዊ ምክንያት በፖለቲካዊ አላማ ለሚያስሩ ሀገራት ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም በማሰሩ ሂደት ውስጥ የተሳተፉ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣልን ሊያካትት ይችላል።
ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ባልተረጋጋበት፣ መንግስትም በአካባቢዎቹ “ህግ የማስከበር” ዘመቻ እያካሄድኩ ነው በሚልበት ወቅት ነው።
በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ፣ በተለይ የኢትዮጵያ ትውልድ ያላቸው አሜሪካውያን ዜጎች ወደ ክልሎቹ ሲጓዙ በቀላሉ በተጠርጣሪነት ሊያዙ እንደሚችሉ ስጋት በመኖሩ ነው ተብሏል።
የኤምባሲው መልዕክትም እንዲህ አይነቱ እስር በአሜሪካ መንግስት እንደ “በግፍ መታሰር” ሊቆጠር እንደሚችል የሚያስጠነቅቅ ነው።
የኤምባሲው መልዕክት በአሜሪካ እና በመንግስታት መካከል ሊኖር ስለሚችል የዲፕሎማሲ ውጥረት ፍንጭ የሚሰጥ ሲሆን፣ ወደ “የትኛውም ሃገር” የሚጓዙ አሜሪካውያን ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግልጽ ጥሪ አቅርቧል።