አፍሪካ
በማዕከላዊ ሱዳን በጎርፍ ምክንያት ከ4,000 በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች መውደማቸው ተነገረ

ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/01/2018፡- በማዕከላዊ ሱዳን አልጃዚራህ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ኡም አልቁራ አከባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ4,200 በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ 550 ቤቶች መውደማቸውን የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ።
የጎርፍ አደጋው ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ዕለት በምስራቃዊ አልጃዚራህ ግዛት የሚገኙ መንደሮችን ያጠቃ ሲሆን 850 አባዎራወች ወይም 4,250 ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸውን የፍልሰተኞች ድርጅቱ ትናንት እሁድ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በተጨማሪም 550 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ በአደጋው የተፈናቀሉ ሰዎችም አቅራቢያ ባሉ ክፍት ቦታዎች መጠለላቸውን ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
በሱዳን ከሰኔ ወር አንስቶ እስከ ጥቅምት ወር ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከባድ ዝናብ የሚስተዋል ሲሆን ይህም ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ክስተትን እያስከተለ ይገኛል።
በሱዳን የተፈጥሮ አደጋ መከሰቱ የተሰማው ሀገሪቱ ከጎርጎሮሳውያኑ 2023 ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል እየተካሄደ የሚገኘው የእርስ በርስ ጦርነት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ነው። ጦርነቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት ሲዳርግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ አፈናቅሏል።