
ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/01/2018፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከቻይናው የምክር ቤት አባልና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ዋንግ ዚያኦሆንግ ጋር ትናንት እሁድ ቤጂንግ ላይ ተገናኝተው መወያየታቸው ተገለጸ።
በውይይታቸውም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ቻይና ላደረገችው “የረዥም ጊዜ ድጋፍና እገዛ” ምስጋና አቅርበው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቻይና ዜጎች፣ ተቋማት እና ፕሮጀክቶችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።
የቻይናው የምክር ቤት አባልና የህዝብ ደህንነት ሚኒስቴር ዋንግ በበኩላቸው፣ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የደረሱበትን ስምምነት መሰረት በማድረግ፣ ሁለቱም ወገኖች “ለ’ቤልት ኤንድ ሮድ’ ፕሮጀክቶች የጸጥታና ደህንነት ትብብራቸውን እንዲያሳድጉ እንዲሁም ወንጀልን የመከላከል አቅማቸውን ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ” ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በሊያንዩንጋንግ በሚካሄደው የ2025 ፎረም ላይ ለመካፈል ወደ ቻይና ማቅናታቸውን ዢንዋ ዘግቧል።