“ምንም የተኩስ አቁም አንፈልግም፣ ችግሩን እኛው ራሳችን እንወጣዋለን” ሲሉ ጄኔራል አልብሩሀን ገለፁ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 05/01/2018፡- በሱዳን ተኩስ አቁም እንዲረግ በአሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሳኡዲ አረቢያና ዩናይትድ አረብ ኤመሬትስ አዲስ ጥረት መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
እነዚህ 4 አገራት ባወጡት የጋራ መግለጫም ለ3 ወራት የሰብአዊነት ተኩስ አቁም እንዲረግ ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን በሚቀጥሉት 9 ወራት ውስጥ ደግሞ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግና በሲቪል የሚመራ መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡
ይህንን ሀሳብ በሌተና ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልብሩሀን የሚመራው የሱዳን መንግስት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለው መግለፁም አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ የጄኔራል አልብሩሀን መንግስት ዛሬ ይህንን አቋሙን መቀየሩን አስታውቋል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ እንደማይገባም አስረድቷል፡፡ የአልብሩሀን መንግስት አቋሙን ለመቀየር የተገደደው ተቀናቃኙ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ዛሬ የድሮን ጥቃት በመሰንዘሩ ነው፡፡
የጄኔራል ሀምዳን ዳጋሎ ሀይሎች በዛሬው እለት በኋይት ናይል ግዛት ውስጥ በርካታ ድሮኖችን በመላክ በሀይል ማመንጫ ጣቢያ፣ በነዳጅ ዴፖና በአየር ማረፊያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ማድረጋቸውን የጠቀሰው የጄኔራል አልብሩሀን መንግስት መግለጫ ጨምሮም ከእነዚህ ድሮኖች አብዛኛዎቹን ለመከላከል መቻሉን አስረድቷል፡፡
መግለጫው ሲቀጥልም ‹‹በ4ቱ አገራት የሰላም ጥሪ ከቀረበ ከሰአታት በኋላ ታጣቂው አማፂ ሀይል ይህንን ጥቃት መሰንዘሩ እያደረገ ባለው ሽብር ለመቀጠል ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው›› ብሏል፡፡
በመሆኑም በ4ቱ አገራት የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበል የጠቀሰው መግለጫው ጨምሮም ‹‹ይህ ጦርነት የታወጀው በሱዳን ህዝቦች ላይ ነው፡፡
ስለዚህም ያለምንም የውጭ ሀይል ድጋፍ እኛው ራሳችን እንወጣዋለን›› በማለት አስታውቋል፡፡