የሱዳን ጦር የሰሜን ኮርዶፋን ከተማ ባራ ከፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሐይል መልሶ መቆጣጠሩን ይፋ አደረገ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/01/2017፡- የሱዳን ጦር እና አጋሮቹ በሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ የምትገኝ የባራ ከተማን ከፓራሚሊተሪ ፈጣን ድጋፍ ሃይሎች ከባድ ውጊያ በኋላ መልሰው መቆጣታቸውን ተናግረዋል።
RSF በሚያዝያ 2023 ከጀመረው ግጭት የመጀመሪያዎቹ ወራት ጀምሮ የግዛቱን ዋና ከተማ ኤል-ኦቤይድን ለማጥቃት እና ከምእራብ ሱዳን በሚወስደው መንገድ ላይ እንደ ቁልፍ ነጥብ በመጠቀም ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የምትገኝ ከተማን ተቆጣጥሮ ቆይቷል።
የ ኤል-ኦበይድ ከተማን መቆጣጠር ከኦምዱርማን ጋር ግንኙነቱን ለመፍጠርም ትልቅ ፋይዳ ይኖሯል።
የሱዳን ሠራዊት ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ “ጦራችን በኃይል፣ በቁርጠኝነት እና በችሎታ ወደ ባራ ከተማ መግባቱን ዛሬ እናስታውቃችኋለን፣ ከተሟ ከርኩሶችና ቆሻሾችን ፀድታለች” ብሏል።
ጦር ኃይሉ ሱዳንን በሙሉ “ከታጣቂዎች፣ ቅጥረኞች እና ተላላኪዎች ቆሻሻ” ለማጽዳት ቆርጦ ተነስቷል ሲል አክሏል።
የመንግስት ወታደሮች እና ተባባሪ ሃይሎች በከተማው ውስጥ ተሰማርተው የሚያሳዩ እና የከተሟ ህዝብም ደስታውን ሲገልፅ የሚያሳይ ቪዲዮዎችን ሲሰራጩ ታይቷል።
ሰራዊቱ በርካታ የወደሙ ተሽከርካሪዎችን አሳይቶ በደርዘን የሚቆጠሩ የRSF ተዋጊዎችን መግደሉን እና መያዙን ተናግሯል።
ጦርነቱ ግን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን እየተገለፀ ነው።
የሱዳን ዶክተሮች ኔትዎርክ ገለልተኛ የሕክምና ቡድን እንደዘገበው በባራ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ሦስት ሰላማዊ ሰዎች ሲሞቱ 14 ሰዎች ቆስለዋል።
ኔትወርኩ ባወጣው መግለጫ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ማነጣጠር “የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግን በግልፅ መጣስ ነው” በማለት በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት ሲቪሎችን እንዲጠብቁ እና ያለ ምንም እንቅፋት የእርዳታ አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቋል።
የሰሜን ኮርዶፋን ገዥ አብደል-ካሌቅ አብደል-ላቲፍ ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር ሲያደርጉ ድሉን “ለሱዳን ህዝብ ስጦታ” ነው ብሏል።
ከደቡብ ሱዳን በመጡ ቅጥረኞች የሚደገፈው RSF ባራ በተቆጣጠረበት ወቅት ያደረሰውን ግፍ እና ዘረፋ እና መኖሪያ ቤቶችን በግዳጅ በመቀማት በርካታ ቤተሰቦች ወደ ኤል-ኦበይድ እንዲፈናቀሉ አድርጓል ሲሉ ነዋሪዎች ከሰዋል።