የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር በነፍስ ማጥፋት እና በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰሱ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/01/2017፡- የደቡብ ሱዳን ቀዳማዊ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የጎሳ ታጣቂዎች በፌደራል ኃይሎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት ተሳትፎ አላቸው በሚል ተጠርጥረው በነፍስ ግድያ፣ በአገር ክህደት እና በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ክስ እንደተመሰረተባቸው የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቀዋል።
ሚኒስቴሩ መግለጫውን ከሰጠ ከሰዓታት በኋላ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸውን ሪክ ማቻርን ከስልጣን ማገዳቸውን የሚገልጽ መግለጫ በመንግስታዊ ሬድዮ የተነበበ ሲሆን፣ ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም ተብሏል።
በማቻር ላይ የቀረበው ይህ ክስ እንዲሁም እሱን ተከትሎ የተሰማው ከስልጣን የመታገዳቸው ዜና በሀገሪቱ በሚንቀሳቀሱት ሁለቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ግጭቶች ይባባሳሉ የሚል ስጋት መፍጠሩን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ከጎርጎሮሳውያኑ 2013-2018 ድረስ የእርስ በርስ ጦርነት ያደረጉ ሲሆን፣ በወቅቱ 400,000 የሚጠጉ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል።
ኪር በተጨማሪ ከሪክ ማቻር ጋር አብረው ክስ የተመሰረተባቸውን የሀገሪቱን የነዳጅ ሚኒስትር ፑኦት ካንግ ቾልንም ከስልጣን ማገዳቸው ተሰምቷል።
የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ናስር ከተማ በዋይት አርሚ ሚሊሻዎች በተፈፀመ ጥቃት ጋር በተያያዘ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ።