አፍሪካኢትዮጵያኢኮኖሚ

ታላቁ ህዳሴ ግድብ – የኢትዮጵያዊያን የፅናት ከፍታ – የአፍሪካ ኢነርጂ አብዮት

ኢትዮ ሞኒተር፡ 04/13/2017፡- መጋቢት 24ም ጳጉሜን 4ም በኢትዮጵያዊያን ልብ ልዩ ስፍራ የሚኖራቸው ቀናቶች ናቸው።

አንዱ ለዘመናት የተፈጥሮ ሃብታችን እንዳንጠቀም የተከለከልንበት ቀንበር የሰበረ ሌላኛው ደግሞ የአይችሉም የተሳሳተ አስተሳሰብ የቀበረ ዕለት።

ኢትዮጵያዊያን አንዱ ዘር የዘሩበት፣ ሌላኛውን ፍሬ አፍርቶ ያፈሱበት ቀናቶች ናቸው።

ይህ የ14 ዓመታት የውጣ ውረድ ጉዞ፣ ይህ የከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤት፣ ይህ የመላው ኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ታላቁ የህዳሴ ግድብ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰማይ ላይ የዘለአለም ሐወልት ሆኖ ቆሟል።

145 ሜትር ከፍታ፤ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ፣ 5 ሺሕ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው፣ 74 ትሪሊዮን ሊትር ውሃ የሚይዘው ታላቁ ግድብ አሁን ተጠናቋል።

ይህ ከሊስትሮ እስከ ቀን ሰራተኛ፣ ከመንግስት እስከ ግል ሰራተኛ፣ ከባለሃብት እስከ ደሃ፣ ከባለ ስልጣን እስከ ተራው ህዝብ መቀነቱን ፈትቶ ያስገነባው ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ 233 ቢሊዮን ብር ወጪ ጠይቋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ እና የእምነት፣ የኑሮ ደረጃና የጤና ሁኔታ፣ የሞያ ዘርፍና የአከባቢ ልዩነት ሳይገድባቸው በጋራ ፍፃሜውን ያደረሱት ግድብ እነሆ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቆ ለኢትዮጵያዊያን የብርሃን ፍንጣቂ ሊያበስር ለአፍሪካዊያን የኢኮኖሚ ትስስር ሊፈጥር ደረስኩላችሁ ብሏል።

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በሰማያዊው አባይ ላይ በይፋ ተመርቋል። ይህ በእውነት አስደናቂ ስኬት ነው።

በአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ፣ የቻይናውን ትልቁን የሶስት ጎርጅስ ግድብ እንኳን ሳይቀር ያስናቀ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የማያዝ አቅም ሲኖረው 39.3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዘውን የሶስት ጎርጅስ ግድብ በእጥፍ የሚበልጠው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም ኩራት ነው።

በቀጣናው ላይ የኢትዮጵያን የኃይል የበላይነት ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት እንደ ኬንያ እና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ ለመጨመር፣ ቀይ ባህርን አቋርጦ ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እንደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሸጥ የማስተላለፊያ መረብ የመገንባት አላማ ያለው ግድብ ነው።

አንድ ሰው በስኬቱ መደነቅ እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። በ2003 ዓ/ም የቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ፕሮጀክት X” ብለው የሚጠሩትን ግድብ ለመገንባት እቅድ በማውጣት ግብፅ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ “የቪቶ ስልጣኗን” እንድታጣ ያደረገ ሂደት የመጀመርያ መርዶ ነበር።

ድሉ ከዚህ ነበር የሚጀምረው። ከዚህ ግዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱን ከዳር ለማድረስ ትልቅ እንቅፋት ገጥሟታል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታገኝ እንዲሁም ውስጣዊ መረጋጋት እንዳይኖራትና ትኩረቷ በግድቡ እንዳታደርግ ያልተሰራ ሴራ አልነበረም።

ይህ በተለይ በግብፅ በኩል የነበረው ጥረት አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ነበር የገለፁት።

“ግብፅ እንደ አለም ባንክ ያሉ ተቋማት ለግድቡ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ እንዳይሰጡ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኝነትን ያጠናከረ ሲሆን ኢትዮጵያ ከዜጎቿ ገንዘብ ለማሰባሰብ ትልቅ እንቅስቃሴ ጀምራለች” ነበር ያሉት።

ሆኖም ከመለስ በኃላ የተረከቡት ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ለተቀሩት ሰባት ዓመታት ያስቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህ ፈተና በሚገባ አልፎታል።

የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህን ፈተና በመጠኑም ቢሆን አንፀባርቆታል።

“የምንኖሩበት ዘመን ቁማር ቤቶች እንኳን ብድር በሚያገኙበት ዓለም ውስጥ ቢሆንም ኃይል ለማመንጨት ድጋፍ ስንጠይቅ ፋይናንስ ተነፍገናል” በማለት ነበር ፈተናውን የገለፁት።

ይህ ፈተና ግን ኢትዮጵያዊያን ግድቡ ከመገንባት አላገዳቸውም። ይልቁንም
ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ክልከላውን ሳይበግራቸው ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ራሳቸው ከኪሳቸው እንዲያዋጡ አደረጋቸው።

በዚህም ኢትዮጵያውያን በቦንድ ሽያጭ ከ20.2 ቢሊዮን ብር (159.9 ሚሊዮን ዶላር) በላይ የሰበሰቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ብር (79,190 ዶላር) አበርክቷል።

ለዚህ ነው እንግዲህ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የላብም የደምም ጠብታ ነው የሚባለዉ።

የላቡ ጠብታ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከትልቅ እስከ ትንሽ ያበረከተው ድጋፍ ሲሆን የደም ጠብታ ደግሞ ህይወት የተከፈለበት በመሆኑም ጭምር ነው።

እዚህ ላይ የሰው ልጅ ህይወት የተከፈለበት ግድብ መሆኑ መረሳት የለበትም።

ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት አረጋግጠዋል። “አዎ እውነት ነው” ሲሉ ሚኒስቴሩ 15,000 ኢትዮጵያውያን በግድቡ ግንባታ 14 ዓመታት ውስጥ መሞታቸውን ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለዚህም ነው ግድቡ የደስታም የሐዘንም ፕሮጀክት የማያደርገው። ለዚህም ነው መታሰብያነቱም ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ እነ ኢንጅነር ስመኘው በቀለን ጨምሮ ህይወታቸውን ላጡት ዜጎች መሆን አለበት የሚሉ ድምፆች የሚሰሙት።

ግድቡ መጀመሪያ ላይ በ16 ተርባይኖች 6450 ሜጋ ዋት ሐይል እንድያመነጭ ታስቦ የተጀመረ ቢሆንም አሁን ተርባይኑ ወደ 13 የማመንጨት አቅሙ 1300 ሜጋ ዋት ቀንሶ ወደ 5150 ሜጋ ዋት እንዲወርድ ተደርጓል።

ያም ሆኖ ይህ ኢትዮጵያዊያን ለ14 ዓመታትን ያረገዙት ግድብ ዛሬ ጳጉሜን 4 አምጦ ወልዶታል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ተመርቋል።

የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት የምረቃ ሥነ ሥርዓት በጉባ በመካሄድበት በዚህ የደስታና የቁጭት ስሜት የታየበት ዕለት በርካታ አፍሪካዊያን ታድሞበታል።

በዚህም ይፋዊ የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዴትን ጨምሮ፤ የሀገሪቱ ከፍተኛ ሚኒስቴሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሆኖም የግብዣ ጥሪ የተደረገላቸው የኡጓንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በምርቃቱ አልተገኙም።

የግብፅና የሱዳን መሪዎች ለሁለቱም አገሮች ጭምር በሚጠቅመው የህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ እንዲገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ጥሪ ብያደርጉላቸውም ህዳሴ ግድብን በድምቀት ሲመረቅ ማዶ ሆኖ እንዲመለከቱ ተገዷል።

በአንድ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀኝ እጅ የነበሩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቅም በዚያን ወቅት የጎበኙትን ታላቁ የህዳሴ ግድብን ሲመረቅ ጉባ ላይ አልተገኙም።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ መመረቁ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሐይል አቅርቦት ከዕጥፍ በላይ ያሳድጓል።

በዚህም የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ሞተር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ አገራትም በመሰረተ ልማት እንዲተሳሱሩ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።

ለዚህም ነው የዓለም ሚድያዎች የአፍሪካ የኢነርጂ አብዮት በኢትዮጵያ ተጀመረ በማለት እየዘገቡት የሚገኙት።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates