አፍሪካየአየር ንብረት አካባቢ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ እቅዶችን በተጨባጭ ተግባራት እያሳየች መሆኗ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 30/12/2017፡- በጉባኤው መክፈቻ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት 4 በመቶ ብቻ ድርሻ ያላት አፍሪካ የከፋውን ጉዳት እያስተናገደች ነው።
ዓለማችን በተለይም አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ፈተና የተወጠረችበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩ ኢኮኖሚያችንን እየፈተነ በነገ ዋስትናችን ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ድርቅ፣ ጎርፍ፣ እያደገ የመጣ የምግብ ዋስትና ችግር እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጣ ፍልሰት የከበቡን ፈተናዎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
አፍሪካ ተጋላጭ ብቻ ሳትሆን ተስፋ ያላትም መሆኑን ያስገነዘቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከ60 በመቶ በላይ ሕዝቧ ከ25 ዓመት በታች የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙላት የወጣቶች አኅጉር ናት ብለዋል።
የአፍሪካ ልጆች በፈጠራዎቻቸው፣ በክህሎታቸው እና በትጋታቸው መፍትሔ አመንጭዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለው ተጨባጭ የአየር ንብረት ለውጥ ስራ ተግባር እና ህልም በማገናኘት ውጤት ለማሳየት መሰራቱን አስረድተዋል።
በ2011 ዓ.ም በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በየዓመቱ ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በማንቀሳቀስ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ እየተተከለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።