ለረጅም ግዜ ከሚድያ የጠፉት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ትላንት በካምፓላ ታዩ።
የኡጋንዳ ልማት ባንክ ያዘጋጀው የፋይናንስ ጉባኤ ትናንት በካምፓላ ተጀምሯል፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/12/2017፡- በጉባኤው ተናጋሪ እንዲሆኑ ከተጋበዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል ለረጅም ጊዜ ከሚድያ የጠፉት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ አንዱ ናቸው።
ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ ያደረጉት ዶክተር አርከበ እቁባይ ልምዳቸው ባካፈሉበት ወቅት እንዳሉት “በ2050 የአፍሪካ ህዝብ ብዛት ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ይደርሳል፡፡ በ2100 ደግሞ ወደ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ይገባል” ብሏል።
ለዚህ ሁሉ ህዝብ የስራ እድል ለመፍጠር ኢንዱስትሪን ማስፋፋት፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው አገልግሎቶችን ማቅረብና ግብርናውን ማዘመን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ግልፅ በሆነ መስፈርት ላይ መመርኮዝና የውጭ ንግድን ታሳቢ ማድረግ እንደሚኖርበት የገለፁት ዶክተር አርከበ ለዚህም የኢትዮጵያን ልምድ እንደተሞክሮ አንስተዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ በሀዋሳ የሚገኘውን ልዩ የኢንዱስትሪ ዞንን የገነባነው በ9 ወራት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ዞን በ3 አመታት ጊዜ ውስጥ ለ35 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር ችሏል” በማለት አብራርቷል፡፡
“እንዲሁም በአጭር ጊዜ የአገሪቱ ትልቁ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመሆን የበቃ ሲሆን ይህም በአላማ ላይ የተመረኮዘ ኢንቨስትመንት ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ማሳያ ሆኗል”በማለት በስልጣን ዘመናቸው ያከናወኑትን ስራ አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል የልማት ባንክ በባህሪው ማተኮር ያለበት በስትራቴጂና ፖሊሲዎች ላይ መሆኑን ያወሱት ዶክተር አርከበ የአፍሪካ ልማት ባንኮች ግን በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት ልክ እንደንግድ ባንኮች መሆኑን ጠቅሰው ይህ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አፍሪካ የለጋሾችን በር ማንኳኳት ያለባት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ መሆን እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡