
ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/12/2017፡- በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን የዳርፉር ግዛት በምትገኝ አንድ መንደር ላይ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከአንድ ሰው በስተቀር ሁሉም የመንደሯ ነዋሪዎች መሞታቸውን የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ አስታወቋል።
አካባቢውን የሚቆጣጠረው ቡድኑ ትናንት ሰኞ ምሽት ላይ እንደገለፀው፣ በሱዳን ምዕራባዊ የዳርፉር ግዛት በደረሰው አደጋ አንድ ተራራማ መንደር ተደርምሶ ከ1,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በሕይወት የተረፈው ደግሞ አንድ ሰው ብቻ ነው። ቡድኑ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም አደጋው የደረሰው ለቀናት ከዘነበው ከባድ ዝናብ በኋላ መሆኑን የጠቆመው ቡድኑ፣ በማራ ተራሮች የሚገኘውን ታራሲን የተባለውን መንደር ማውደሙን ገልጿል።
እስከአሁን ባለው መረጃም ከአንድ ሰው በስተቀረ ሁሉም የመንደሩ ነዋሪዎች ህይወት ማለፉን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የመሬት መንሸራተት አደጋው “በጣም ከፍተኛ እና አውዳሚ” እንደነበር የተገለጸ ሲሆን አካባቢው በብዛት የሎሚ ምርት የሚመረትበት እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል።