“በኢትዮጵያዊያን ላይ ጥቃት ያደረሱትን በሙሉ ለህግ እናቀርባቸዋለን” ሲሉ የሱማሊላንድ ፕሬዝደንት ተናገሩ፡፡

ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/12/2017፡- በሱማሊላንድ ሀርጌሳ ከተማ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያዊያን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን ይታወሳል፡፡
በዚህ ጥቃትም ከ150 በላይ ኢትዮጵያዊያን በዱላና በሌሎችም መንገዶች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተገልፆ ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የሱማሊላንድ ፕሬዝደንት አብዲራሂም መሀመድ አብዱላሂ ኤሮ በሰጡት መግለጫ “ሶማሊላንድ የምትታወቀው በእንግዳ ተቀባይነቷ፣ በሉአላዊነቷና ለሁሉም ክብር የምትሰጥ በመሆኗ ነው”ብለዋል፡፡
እንዲሁም “ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ስር የሰደደ እና ታሪካዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያዊያን ላይ ብቻም ሳይሆን በማንኛውም የውጭ ዜጋ ላይ የቃላትም ሆነ ሌላ የትኛውም አይነት ጥቃት ማድረግ ተቀባይነት የሌለው ነው” በማለት አሳስቧል።
የሶማሊላንድ የፀጥታ ሀይሎች ለሁሉም የውጭ ዜጎች ጥበቃ መስጠትን ቅድሚያ እንዲሰጡ ትእዛዝ ያስተላሉፉት ፕሬዝዳንቱ በተለይ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ላይ ልዩ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
“ማንኛውም ዜጋ ከህግ በላይ ሊሆን ወይንም የደቦ ፍርድ ሊሰጥ አይችልም፡፡ ግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ በአገራችን ውስጥ ቢኖሩም ሆነ ወንጀል ቢሰሩ እንኳ ይህንን ጉዳይ መመልከት ያለባቸው የፀጥታና የፍትህ አካላት ብቻ ናቸው፡” ያሉት ፕሬዝደንቱ በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃትና ትንኮሳ የፈፀሙ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡
በሰሞኑ በኢትዮጵያዊያን ጥቃት ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በሙሉ በህግ ተጠያቂ ሆነው ተገቢውን ቅጣት እንደሚያገኙም ቃል ገብተዋል፡፡