
ኢትዮ ሞኒተር፡ 27/12/2017፡- በሕገ-ወጥ መንገድ ዜጎችን ወደ ውጪ ሀገራት ሲልኩ የተገኙ 350 ሕገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።
እርምጃው ከሦስት ወር የሥራ ማገድ ጀምሮ እስከ ንግድ ፍቃድን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ የሚያካትት መሆኑን ተገልጿል፡፡
በዚህም “በሦስት ወር ውስጥ ብቻ 350 የሚሆኑ ሕገ-ወጥ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪት ላይ ሲሰሩ በመገኘታቸው እርምጃው ተወስዶባቸዋል” ብለዋል።
በመንግሥት እውቅና ተሰጥቷቸው ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር እንዲያሰማሩ ፍቃድ ያላቸው 1 ሺሕ 286 የሚሆኑ አጀንሲዎች መኖራቸውን፤ “እነርሱ ሕገ-ወጥ ተግባራትን እንዳያከናውኑ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በእነሱም ላይ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል” ሲል አብራርቷል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኤጀንሲዎቹ ላይ በሁለት መንገድ ቁጥጥር እንደሚያደርግ የተገለፀ ሲሆን፤ ዜጎች ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት የጉዞ ሰነዳቸውን ፕሮሰስ በሚያደርጉበት ጊዜ በተፈቀደላቸው ሀገር ብቻ ዜጎችን እንዲያሰማሩ የሚያስችል ክትትል እንዲሁም፣ ዜጎች ከሀገር ከወጡ በኋላ ተገቢውን ከለላ እንዲደረግላቸው አጀንዳዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር መሆናቸውን አስታውቋል።
በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሰማርተው በሚሰሩ ኤጀንሲዎች ላይ ያለምን ቅድመ ሁኔታ እርምጃ መውሰድን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም የአሐዱ ዘገባ ያመለክታል።