“የቀኝ ግዛት አስተሳሰቦች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በተያዘለት ቀን ታስመርቃለች ብሏል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 22/12/2017፡- የቀኝ ግዛት አስተሳሰቦች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተያዘለት ቀን እንደምታስመርቅም ሚኒስቴሩ በመግለጫ ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ሳምንታዊ መግለጫው ትኩረት ያደረገው ሀገሪቱ በምታካሂዳቸው ሰሞነኛ ሁነቶች ዙሪያ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ኢትይጵያ በቅርቡ ካሪኮም (የአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት) ጉባኤ እና የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን እንደምታስተናግድ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው አስታውቀዋል።
ሌላው የመግለጫው ትኩረት የነበረው ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሲሆን፤ “ሀብቱ የተፋሰስ ሀገራት ሀብት በመሆኑ በጋራ ለመጠቀም ኢትዮጵያ ሁሌም ትሰራለች” ሲሉ ገልጸዋል።
“የሕዳሴው ግድብ ስላለቀ ብቻ የሚቆም አይደለም” ያሉት አምባሳደሩ፤ የዲፕሎማሲ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ በጎ የሚመኙ የሚያከብሩትና በምረቃው ላይ የሚገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር ነብያት ይህንን የገለጹት ‘በግድቡ ምረቃ ወቅቅተ የተጋበዙ ሰዎች እና ሀገራት ማን እንደሆኑ’ በተጠየቁበት ወቅት ነው። አምባሳደሩም “ከግብዣው ጋር በተያያዘ ጊዜው ሲቃረብ የሚታይ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ይህ ግድብ ከማንም በላይ የኢትዮጵያውያን በመሆኑም የምረቃው ዕለትም የኢትዮጵያውን ነው የሚሆነው” ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።