በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በፖለቲካዊ ጫና፣ በደህንነት ስጋቶች እንዲሁም በሙያ ሥነ-ምግባር እየተፈተኑ ነው ሲል አንድ ጥናት አመላከተ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 22/12/2017፡- በአለማችን ጋዜጠኞች ለከፍተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ሙያዊ ነፃነታቸው ተገፎ አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ከሚፈጸምባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አንድ ጥናት አመላከተ፤ ከሙያቸው የሚጠበቅባቸውን ሥነ-ምግባር ለመተግበር እየተፈተኑ ነው ብሏል።
በጎርጎሮሳውያኑ 2023/24 የዓለም የጋዜጠኝነት ጥናት (WJS) አካል የሆኑ 363 ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ላይ በተደረገው ጥናት፣ 26.7 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት አምስት ዓመታት በእስር ላይ እንደነበሩ ወይም ታስረው መፈታታቸውን ገልጸዋል። ተርየ ስካርዳል በተባለ ተመራማሪ የተዘጋጀውና የፎጆ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ባደረገው አዲስ ጥናት ይህ ውጤት በአለምአቀፉ ደረጃ አማካኝ ከሆነው የ3.7 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በጣም የላቀ ነው ተብሏል።
በ60 ጋዜጠኞች ላይ በተደረገው ቃለ መጠይቅ የተመሠረተው ጥናቱ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተዋናዮች የሚፈጸሙ ዛቻዎች፣ እስር እና የትንኮሳ ድርጊቶች የመገናኛ ብዙኃን ደኅንነትን ስጋት ላይ ጥሏል ሲል አስጠንቅቋል።
በአማራ፣በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ባሉና በግጭቶች ስር ሆነው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ከፍተኛውን አደጋ እንደሚጋፈጡም ተረጋግጧል።
የኤልፋሸር፣ ሱዳን ህጻናት ከ500 ቀናት ከበባ በኋላ ‘በረሃብ አለንጋ’ እየሞቱ ነው ሲል ዩኒሴፍ አስታወቀ።
በሱዳን ሰሜናዊ ዳርፉር የምትገኘው ኤል ፋሸር ከተማ ከ17 ወራት ያህል ከበባ በኋላ “የህፃናት የስቃይ ማዕከል” ሆናለች፣ ሲል የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስጠንቅቋል።
በቅርብ ወራት ውስጥ ቢያንስ 600,000 ሰዎች ግማሾቹ ህጻናት ከኤልፋሸር ካምፖች እና አከባቢዎች ለመሸሽ ተገድደዋል ብሏል ድርጅቱ።
የሱዳኑ ድጋፊ ሰጪ ሃይሎች (RSF) ከበባ ውስጥ በምትገኘው ኤልፋሻር
ረሃብ፣ ጅምላ መፈናቀል እና የማያባራ ሁከት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገልጿል።
130,000 ህጻናትን ጨምሮ 260,000 የሚገመቱ ንፁሀን ዜጎች በኤል ፋሸር ውስጥ ተከበው ከ16 ወራት በላይ ርዳታ ተቋርጠዋል ሲል ኤጀንሲው ገልጿል።
የዩኒሴፍ ዋና ኃላፊ ካትሪን ራስል “በኤል ፋሸር ውስጥ ያሉ ህጻናት በረሃብ እየተሰቃዩ ነው እና ዩኒሴፍ ህይወት አድን የአመጋገብ አገልግሎት እየተከለከለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የእርዳታ ተደራሽነት መከልከል የህፃናትን መብት መጣስ ነው፣ እናም የህጻናት ህይወት ማዳን የሁሉም ሰው ልጅ ግዴታ መሆን አለበት” ብሏል።