
ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/12/2017፡- በምዕራብ ዕዝ ቴዎድሮስ ኮር 4ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ትላንት በተከበረበት ወቅት ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ የተገኙት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ “በውጭ ያሉ ጠላቶቻችን እና ውስጥ ያሉ ጠላቶቻችን ተሰባስበው እንመጣለን እያሉ ሲመክሩና ሲፎክሩ ይሰማል።
እኛም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመላ ህዝባችን ጋር ሆነን ምን ሊያደርጉ እንደሚመጡ ስለምናስብና ስለምናውቅ ተዘጋጅተን እንጠብቃቸዋለን፤ ያኔ የተለመደውን ዋጋ ከፍለን ኢትዮጵያን ካሰቡላት ጥፋት እንደ ትናንቱ እንታደጋለን” ብለዋል።
እነዛ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ያሉዋቸው እነማን እንደሆኑ ግን በስም አልጠቀሷቸውም።
በህጋዊ መንገድ በህዝብ የተመረጠ መንግስትን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በአፈሙዝ ለማስወገድ የሚደረግ ማናቸውም ሙከራ ጀግናው ሠራዊታችን እያለ አይሳካም ያሉት ጄኔራል አበባው ታደሠ ለህዝብ የሚጠቅም አማራጭ ሃሳብ ያለው ማንኛውም አካል ህጋዊ እና ሠላማዊ መንገዶችን ተጠቅሞ ምኞቱን ለማሳካት መስራት እንደሚችል እና የዘመኑ ብቸኛ አማራጭም ይህ ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቁርጥ ቀን ልጆች እያለን ኢትዮጵያን መበተን አይቻልም፤ አይታሠብምም ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ቴዎድሮስ ኮር አሁን ተሰማርቶበት በሚገኘው የሆሩ ጉድሩ ወለጋ ዞን፤ አሸባሪውን የሸኔን ቡድን በመምታት እና ተገዶ ወደ ሰላም እንዲገባ በማድረግ ለአካባቢው ህዝብ አንፆራዊ ሰላም ማስፈን የቻለ ኮር ነው ሲሉ ገልጿል።