ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በዓለማችን ዝቅተኛ ሰላም ካለባቸው አገራት ተርታ ተመደቡ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 19/12/2017፡- በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት ከሰላም አንጻር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የዓመቱ የዓለም አገራት የሰላም ሁኔታ መዘርዝር አመለከተ።
የአውሮፓውያኑ 2025 ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ (ጂፒአይ) በዓለም ዙሪያ ያሉ የ163 አገራትን የሰላም ሁኔታ በገመገመበት ሪፖርቱ ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዝቅተኛ ነጥብ በማግኘት ከዝርዝሩ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ ከ163 አገራት 25ቱን በመቅደም 138ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ከፍ ብላ 132ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በተጨማሪም በዚህ የሰላም ሁኔታ ግምገማ ውስጥ ከተካተቱት 44 የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ 36ኛ ስትሆን ኤርትራ ደግሞ 32ኛ ደረጃን ይዛለች።
የዓለም አገራትን የሰላም ሁኔታ የሚያሳየውን መዘርዝር ያዘጋጀው የኢኮኖሚ እና ሰላም ተቋም (አይኢፒ) አይስላንድን በዓለም ሰላም የሰፈነባት አገር በማለት ቀዳሚ አድርጓታል።
የዓለም የሰላም መዘርዝር የዓለም አገራትን ሰላም 23 አመላካቾችን ተጠቅሞ የአገራትን የፀጥታ እና የመረጋጋት ሁኔታ ይመዝናል።
ይህ የአገራት የሰላም ሁኔታ ደረጃ የሚወጣው አገራቱ ካላቸው ማኅበረሰባዊ ደኅንነት፣ ከለባቸው የአገር ውስጥ እና የውጭ ግጭት እና ከሚያካሂዱት ወታደራዊ ግንባታ አንጻር ነው።
ሌሎች የአፍሪካ አገራት እና ሰላም በግሎባል ፒስ ኢንዴክስ መስፈርቶች ከአፍሪካ አገራት 26ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ሰላም የሰፈነባት አገር የተባለችው ሞሪሺየስ ስትሆን እርሷን በመከተል በአህጉሪቱ በፖለቲካ መረጋጋት እና ዝቅተኛ የሆነ ግጭት በማስመዝገብ ቦትስዋና፣ ናሚቢያ እና ጋምቢያ ይከተላሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2025 የዓለም ሰላም መዘርዝር 97 የዓለም አገራት ሰላም ያሽቆለቆለባቸው ተብለው ተፈርጀዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የሰላም ማሽቆልቆል ተመዝግቧል።
ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ከ44 የአፍሪካ አገራት ውስጥ 36ቱ በአንድም ወይም በሌላም መንገድ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ሪፖርቱ ተመልክቷል።
ቡርኪና ፋሶ በዓለም ላይ ከፍተኛው የሽብርተኝነት ስጋት ያለባት አገር መሆኗ በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከዓለማችን አስር የሽብርተኝነት ስጋት ካለባቸው አገራት መካከልም ስድስቱ የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ነው።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቀጠናው ዝቅተኛ ሰላም ካለባቸው እና ሰላም በአስከፊ ሁኔታ ካሽቆለቆለባቸው አገራት መካከል ተመድባለች።
በተቃራኒው ኡጋንዳ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ በሰላም ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየች መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
መካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ በ2025 በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ ሰላም ያለባቸው ቀጠናዎች ተብለዋል።
ሱዳን፣ የመን፣ ሶሪያ እና እስራኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም ካጡ 10 አገራት መካከል ተቀምጠዋል።
አይስላንድ፣ አየርላንድ፣ ኒውዚላንድ፣ ኦስትሪያ እንዲሁም ስዊትዘርላንድ የዓለማችን ሰላማዊ አገራት ተብለው ከአንድ እስከ አምስት በቅደም ተከተል ከተቀመጡት አገራት መካከል ናቸው።