
ኢትዮ ሞኒተር፡ 16/12/2017፡- የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በ48 ሰአታት ውስጥ በአባይ ጉዳይ ከ6 የአፍሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ሲወያዩ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ኸደ ሳውዲ ዓረቢያ አምርቷል።
የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብድላቲ እንደገለፁት ከስድስት አገር ሚኒስትሮች ያደረጉት ውይይት በስልክ ነው፡፡
መስሪያ ቤታቸው ባሰራጨው መረጃ ባለፉት 48 ሰአታት ሚኒስትሩ ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልፆ የውይይቱ ዋነኛ አጀንዳ የውሀ ዋስትና ለግብፅ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ማስረዳት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚህ የስልክ ንግግራቸው “ግብፅ የውሀ ዋስትናዋ እንዲረጋገጥ አለም አቀፍ ህግ አንዲከበር ትፈልጋለች” ማለታቸውንም አስረድቷል፡፡
ሚኒስትሩ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ስልክ ለደወሉላቸው ሚኒስትሮች አስታውቀው ነገር ግን በአባይ ወንዝ ላይ የሚደረግን የተናጠል እርምጃ እንደማትቀበል መግለፃቸውን መስሪያ ቤታቸው ጠቅሷል፡፡
ሚኒስትሩ ይህንን ንግግር ያደረጉት በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው ግድብ ሊመረቅ ጥቂት ሳምንታት መቅረቱን ተከትሎ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የግብፁ ፕሬዝደንት አል ሲሲ ከኡጋንዳው አቻቸው ጋር በካይሮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ግብፅ የውሀ ዋስትናዋ አደጋ ላይ ሲወድቅ ዝም ብላ ትመለከታለች ብለው የሚያስቡ ካሉ ተሳስተዋል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ‹”የአባይ ውሀን ጉዳይ ከታሪክ ወጥተን ሰፋ ባለ መነፅር ልንመለከተው ይገባል” ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡
በሌላ ዜና የግብፁ ፕሬዝዳንት በቀይ ባህርና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ለመነጋገር ወደ ሳዑዲ አረቢያ አምርቷል።
የግብፁ ፕሬዝደት አብደልፈታህ ኤልሲሲ ሳዑዲ ሲገቡ የሳዑዲ ልኡል ቢን ሳልማን የተቀበሏቸው ሲሆን ጉብኝታቸው በዋናነት የእስራኤልን በጋዛ ላይ የከፈተችውን ጦርነት ጨምሮ በሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ የመን እና በቀይ ባህር ደህንነት ላይ ስላሉ የቅርብ ጊዜ ቀጠናዊ ሁኔታዎች ውይይት ለማድረግ መሆኑን የሳዑዲ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።