ማህበራዊ
ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ “ለመንገዴ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ተደረገ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 16/12/2017፡- የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በመተባባር ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ “ለመንገዴ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ መደረጉ ተገለፀ፡፡
መተግበሪያው በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎች ከቅድመ ጉዞ በፊት ማድረግ ስለሚኖርባቸው ቅድመ ዝግጅቶች፣ መብትና ግዴታዎቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነቢሃ መሐመድ ገልጸዋል፡፡
መተግበሪያው በራስ አቅም በልጽጎ ወደ ሥራ የገባ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ፤ ይህም በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪቱ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከመረጃዎቹ ባሻገርም ምንም አይነት ቅሬታም ሆነ ችግር በሚገጥማቸው ወቅት ለሚመለከተው አካል በቀላሉ ማሳወቅ እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የዓለም የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኩምቡላ ዳባ በበኩላቸው፤ መተግበሪያው መልከ ብዙ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው መሰል ሥራዎችን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ይሰራል ብለዋል።
በተጨማሪም መተግበሪያው በአማርኛ፣ በአረብኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በቴሌብር ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።