መካከለኛ ምስራቅ

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ማጥቃት መጀመሩን አስታወቀ

ኢትዮ ሞኒተር፡ 15/12/2017፡- የእስራኤል ጦር የጋዛ ከተማን ሙሉ በሙሉ ለመያዝ እና ለመውረር በማቀድ “የመጀመሪያ እርምጃ” ያለውን የምድር ጥቃት መጀመሩን ተናገረ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትስ ማክሰኞ ዕለት ያፀደቁት እና በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ለፀጥታው ካቢኔ እንደሚቀርብ ለሚጠበቀው ዕቅድ መሠረት ለመጣል የአገሪቱ ወታደሮች በዘይቶን እና ጃባሊያ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የጦሩ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

በምድር ውጊያው ላይ በቀጥታ የሚሳተፉ ወታደሮች በዘመቻው ላይ እንዲያተኩሩ ወደ 60,000 የሚጠጉ ተጠባባቂ ኃይሎች በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ሐማስ እስራኤል “በንፁኃን ዜጎች ላይ የምታካሄደውን አረመኔያዊ ጦርነት” ለመቀጠል የተኩስ አቁም ስምምነቱን አደናቅፋለች ሲል መወንጀሉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በጋዛ ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለቅቀው እንዲወጡ እና በደቡብ ጋዛ ወደሚገኘው መጠለያ እንደሚያመሩ ይታዘዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ረቡዕ ዕለት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ሁለቱንም ሕዝቦች ወደ ቀውስ እንዲሁም አጠቃላይ ቀጠናውን ወደ ማያባራ የጦርነት አዙሪት ውስጥ የመክተት አደጋ አለው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በበኩሉ ተጨማሪ መፈናቀል እና የእርስ በርስ ግጭት መባባስ በጋዛ 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ “አሁን ያለውን አስከፊ ሁኔታ ሊያባብስ ይችላል” ብሏል።

ባለፈው ወር የእስራኤል መንግሥት ከሐማስ ጋር በተዘዋዋሪ እያደረገ የነበረው የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ውጤት ሳያስገኝ ከቀረ በኋላ መላውን የጋዛ ሰርጥ የመውረር ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።

ረቡዕ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ኤፊ ደፍሪን በቴሌቭዥን በተላለፈ መግለጫቸው ላይ ሐማስ ከ22 ወራት ጦርነት በኋላ “ተመትቷል እንዲሁም ተጎድቷል” ብለዋል።

አክለውም “የአሸባሪው ድርጅት የመንግሥት እና ወታደራዊ ሽብር ምሽግ በሆነችው በጋዛ ከተማ በሐማስ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ ተደምጧል።

“ከመሬት በላይ እና በታች ባሉ የሽብር መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በማጠናከር ሕዝቡ በሐማስ ላይ ያለውን ጥገኝነት እናቋርጣለን” ብሏል።

“የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ ጀምረናል፤ እናም አሁን የእስራኤል ወታደሮች የጋዛ ከተማን ዳርቻ እየተቆጣጠሩ ነው” በማለት እስራኤል ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እንቀጥል ስቃሴ መጀመሯ ተናግሯል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates