የአየር ንብረት አካባቢ
በሚቀጥሉት 11 ቀናት ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ይኖራል ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስጠነቀቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 15/12/2017፡- የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥሉት 11 ቀናት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት አስተዋጽኦ የሚያርግ ከባድ ዝናብ ይኖራል ሲል ተንብይዋል።
በመደበኛ ሁኔታ በነሐሴ ወር የመጨረሻው 11 ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በበለጠ ሁኔታ እየተጠናከሩ የሚሄዱበት ጊዜ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት በፀሐይ ኃይል ታግዘው ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ለወንዞች ሙላትና ለቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት አስተዋጽኦ የሚያርግ በረዶ የቀላቀለ ከባድ መጠን ያለዉ ዝናብ እንደሚኖር ጠቁሟል፡፡
በዚህም በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን እና መካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚ.ሜ በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የአሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል፡፡
በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትይቱ ጠቁሟል፡፡