ማህበራዊ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ዜጎች ድጋፍ የሚሰጥበትን ስርዓት እንዲያጠናክር ኢሰመጉ ጠየቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 15/12/2017፡- ‎የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ሀገራት በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገኙ የስደት መስመሮች ላይ ላሉ ዜጎች፤ አስፈላጊውን የቆንፅላ ድጋፍ እንዲያደርግና በችግር ላይ ለሚገኙት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበትን ስርዓት እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጠይቋል።

ኢሰመጉ እየተባባሰ የመጣው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደት እያስከተለ ያለው አደጋን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም ኑሮን ለማሻሻል በሚል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በባህር በመጓዝ ዕድል የቀናቸው ያሰቡበት ሀገር ሲደርሱ፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች ደግሞ በውቅያኖስ እና ባህር ላይ ሕይወታቸውን እያጡ እንደሚገኙ አንስቷል፡፡

“የዜጎች ወደተለያዩ ሀገራት መሰደድ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣና በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ለሞት እየዳረገ ይገኛል” ሲልም ገልጿል።

ሐምሌ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በየመን አብያን ግዛት ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በመስጠሟ 68 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መሞታቸውን እና 74 ስደተኞች የደረሱበት አለመታወቁን አንስቷል።

እንዲሁም ካንፋር በተባለ አካባቢ የ54 ስደተኞች አስክሬን በውቅያኖስ ዳር መገኘቱን እንዲሁም የ14 ስደተኞች አስክሬን ሆስፒታል መላኩን እና 12 ሰዎች በሕይወት መትረፋቸውን አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት መግለጹን አስታውሷል።

“መንግሥት እና በስደተኞች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠትና የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በመስራት ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው” ብሏል ኢሰመጉ።

የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች፥ የፀጥታ መደፍረስ፥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ሌሎች አለመረጋጋቶችን እልባት እንዲያገኙ በማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን በማስፈንና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዜጎች በሀገራቸው በሰላምና በክብር የሚኖሩበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቋል።
በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በስደት መስመሮች ላይ ላሉ ዜጎች አስፈላጊውን የቆንፅላ ድጋፍ እንዲያደርግና በችግር ላይ ለሚገኙት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበትን ስርዓት ማጠናከር ይገባል ብሏል።

Show More

Related Articles

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው

  (To Type in English, deselect the checkbox. Read more here)
Back to top button
Lingual Support by India Fascinates