የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የኔታንያሁ የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድ ማፅደቁ ተሰማ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 02/12/2017፡ የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድን አፅድቋል።
ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት እና ከጋዛ አስተዳዳሪነቱ ማስወገድን ጨምሮ አምስት መርሆዎችን ይዟል የተባለው ዕቅድ የፀደቀው በዛሬ ዕሐት ነው።
ውሳኔው የተላለፈው “ከፍተኛ አብላጫ ያላቸው የካቢኔ ሚኒስትሮች ለአማራጭነት የቀረበላቸው ሌላኛው ዕቅድ የሐማስን መሸነፍ ወይም ታጋቾችን መመለስ ማሳካት እንደማይቻል ካመኑ በኋላ መሆኑን” የወጣው መግለጫ ያስረዳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በካቢኔው በአብላጫ ድምጽ የጸደቁ የጋዛ ከተማን ለመውረር እንዲሁም ጦርነቱን የመቋጨት አምስት መርሆዎች የያዘ እቅድ ዘርዘር ያለ መግለጫ አውጥቷል።
አምስቱ ተብለው የተዘረዘሩት መርሆች: ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ ሁሉንም ታጋቾች መመለስ (በህይወት ያሉ እንዲሁም የሞቱትን አስከሬኖቻቸውን)፣ የጋዛን ሰርጥ ከወታደራዊ ትጥቅ ነጻ ማድረግ፣ ጋዛን የሚያስተዳድረውን ሐማስን በማስወገድ እንዲሁም ዌስት ባንክን ከሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ውጭ የሆነ አማራጭ የሲቪል መንግሥት ምስረታን ያካተተ ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ወረራ ዕቅዶቻቸውን በተመለከተ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ” ደህንነታችንን ለማረጋገጥ፣ ሐማስን ለማስወገድ እንዲሁም ህዝቡ ነጻ እንዲሆን የጋዛን አስተዳደር ለሲቪል መንግሥት የማስተላለፍ እቅድ አለን። ይህንን አስተዳደር የሚረከበው ሐማስ ወይም የእስራኤልን መጥፋት የሚደግፍ አይሆንም” ብለዋል።
“ራሳችንን ነጻ አውጥተን የጋዛን ህዝብ ከሐማስ አስከፊ ሽብር ነጻ ማውጣት እንፈልጋለን” ሲሉ የተናገሩት ኔታንያሁ ሆኖም እስራኤል ጋዛን “ጠቅልላ መግዛትም ሆነ እያስተዳደረች መቆየት እንደማትፈልግ” ተናግረዋል።
የእስራኤል ዕቅድ መፅደቅን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ እቅዱ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።
“ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ውሳኔን የሚጻረር ነው፣ እስራኤል ይዞታዋን በተቻለ ፍጥነት እንድታቆም፣ ፍልስጤማውያን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲከበር እጠይቃለሁ” ብሏል ኮሚቴው።