በኤርትራ የተያዘብኝን ገንዘብ በፍርድ ቤት ለማስመለስ ያረኩት ጥረት አልተሳካም ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ

ኢትዮ ሞኒተር፡ 29/11/2017፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በኤርትራ አየር ክልል እየበረረ መሆኑን ገልጾ፤ በኤርትራ ያልተከፈለው የተየዘበት ገንዘብ ግን እስከአሁን እንዳልተመለሰ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርቱን አስመልክቶ፤ በዛሬዉ ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህ በዛሬው መግለጫ ላይ አየር መንገዱ ያለፈው በጀት ዓመት ከሌሎች ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ለየት ያለ ዓመት መሆኑ ተገልጿል።
መግለጫውን የሰጡት የአየር መንገዱ ዋና ስሥ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ በተለይም በዓለም ተለዋዋጭ የፀጥታ ስጋት ተፅዕኖ ውስጥ መውደቁን ገልጸዋል።
የኤርትራ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ እንዳይበር ባገደ ሰሞን፤ አየር መንገዱ ‘ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ያልከፈለኝ ነው’ ያለውን 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍለው መጠየቁ ይታወሳል።
“በፍርድ ቤት ገንዘቡን ለማስመለስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ አዲስ የፓለቲካ ውጥረት በመኖሩ ይሆን ምላሽ ሊሰጡን አልፈቀዱም” ብለዋል።
አየር መንገዱ የሀገር ውስጥ በረራ ለማካሄድ አነስተኛ አውሮፕላኖች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህን ለመፍታት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
“ይህ የ2017 በጀት ዓመት ብዙ ክስተቶች የተከሰቱበት ዓመት ነበር” ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሱዳን፣ በሩሲያ ዩክሬን እንዲሁም በኮንጎ ያሉ የፀጥታ ሁኔታዎች አየር መንገዱ ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠሩበት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አየር መንገዱ በርካታ መዳረሻዎች መጓዙን እና ከፍተኛ ሥራዎች መሰራታቸውን በመግልጽ፤ ከ19 ሚሊዮን በላይ መንገደኛ በአየር መንገዱ መጓጓዝ መቻሉን አስታውቀዋል። በተጨማሪም 785 ሺሕ 323 ቶን በላይ ካርጎ በአየር መንገዱ በኩል መጓጓዙን ተናግረዋል፡፡
በዚህም አየር መንገዱ በዚህ በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም እንደነበረው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በዚህ ዓመት በፀጥታ ምክንያት ወደ አስመራ፣ ፖርት ሱዳን እና ግማ (ኮንጎ) መብረረ አለመቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል።
በዛሬው መግለጫ አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባቱን የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ገቢ ጋር ሲነፃፀር 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ተነግሯል።
እንዲሁም አየር መንገዱ በዓመቱ 6 ዓለም አቀፍ ጣቢያዎች መክፈት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ 13 የተለያዩ አውሮፕላኖች ወደ ሥራ ማስገባቱ ተመላክቷል።