አሜሪካ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀም እጇ እንድታስገባ ህወሓት ጠየቀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 28/11/2017፡ ህወሓት አሜሪካ የስምምነቱ አፈፃፀምን የሚከታተል ልዩ መልእክተኛ እንድትመድብም በደብዳቤ ጠይቋል።
እ.አ.አ. ነሐሴ 2 ቀን 2025 ህወሓት በቀጥታ ለአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩብዮ የፃፈው ደብዳቤ የአሜሪካ አመራር የሰሜን ኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት በአስቸኳይ እንዲመለስ ሚናውን እንዲወጣ የሚጠይቅ ነው።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ሰላም በተለይም በህወሓትና የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ያደረገችው ጥረት ያደንቃል ያለው ደብዳቤው ይህም አሜሪካ ለሰላም፣ ሰብአዊ መብትና ቀጠናዊ መረጋጋት ያላት የማይናወጥ አቋም ያሳያል ይላል።
በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀምና ዳግም ጦርነት እንዳይነሳ ከአሜሪካ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋገጠው ህወሓት ይህ ግንኙነት ወሳኝ የሚያደርገው ለትግራይና ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ለሚኖራት አገራዊ ፍላጎትም ጭምር ነው ብሏል።
በትግራይና የፌደራል መንግስት እየተካረረ የመጣዉን ግንኙነት ዳግም ወደ ግጭት በማምራት ቀጠናውን ከማወክ ባለፈ በትግራይ ህዝብ ላይ ዳግም ጄኖሳይድ የመፈፀም አደጋ እንዳለው ለማርኮ ሩብዮ የተላከው ደብዳቤ ያስረዳል።
በትግራይ ከ2020- 2022 በነበረው በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቁ ደም አፋሳሽ ጦርነት ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ፣ ፆታዊ ዓመፅ፣ ስርዓታዊ ጅምላ ግድያ እና የመሰረተ ልማቶች ውድመትን ያካተተ ጄኖሳይድ እንደተፈፀመ የኒው ላይንስ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ጥናቶች ያረጋገጡት እውነት እንደሆነ ያስታወሰው ህወሓት ይህም በኢትዮጵያ ሰራዊትና እሱን ደግፎ የተሳተፈው የኤርትራ ሰራዊት መፈፀሙ ገልጿል።
ሕዳር 2022 በአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተፈረመውን የፕሪቶሪያ ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲመለሱ ጨምሮ በርካታ ተስፋዎች እንኳን የነበረው ቢሆንም ለስምምነቱ ወሳኝ ሚና የነበራቸው ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሃመር ከተነሱ ጀምሮ ግን የዲፕሎማሲ ክፍተት መፍጠሩን ገልጿል።
የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪዎች የነበራቸውን ሚና እንዳለ ሆኖ የስምምነቱ ቁልፍ አንቀፆችን ማለትም የተፈናቃዮች መመለስና የትግራይ ሕገ መንግስታዊ ግዛትን ከማስጠበቅ አንፃር ግን ወድቋል ያለው የህወሓት ደብዳቤ ይህ ውደቀት ለዘላቂ ሰላምና መተማመን ማጣት ምክንያት መሆኑ አስረድቷል።
በትግራይ ጦርነት ጥምረት ፈጥሮ የነበሩት የኤርትራ እና ኢትዮጵያ መንግስታት አሁን መካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ትግራይን ዳግም የጦረሸ አውድማ እንዳያደርጋት ስጋቱን የገለፀው ህወሓት ይህን ከደገኛ ሁነታ ግምት ውስጥ በማስገባት የአሜሪካ አመራር ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዳይከሰት ወጥረቱን በማርገብና የሰላም ስምምነቱን እንዲፈፀም አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ህወሓት የተጀመረውን የሰላም ሂደት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል አሜሪካ አዲስ የዲፕሎማሲ ልኡክ እንድትመድብም ጠይቋል።
አሜሪካ የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈፃፀም የሚከታተል፣ ውጤታማ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀመር የሚያደርግና ዳግም ግጭት እንዳይቀሰቀስ ከዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ባለ ድርሻ አካላት ሆኖ የሚሰራ ግልፅ ሐላፍነት ያለው ከፍተኛ ልዩ መልእክተኛ እንድትመድብም ህወሓት ማርኮ ሩብዮን ጠይቋል።
የትግራይ ህዝብ ለቀጠናው ሰላም፣ ፍትህ እና መረጋጋት ከአሜሪካ ጋር በቁርኝት እንደሚሰራም ህወሓት በላከው ግልፅ ደብዳቤ አረጋግጧል።