
ኢትዮ ሞኒተር፡ 25/11/2017፡ ለሁለት ዓመታት ተካሂዶ በፕሪቶርያው ስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀል እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ሥነ-ልቦናዊ ጫናን አስከትሏል ያለው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፕሪቶርያው ስምምነት ቁልፍ አንቀጾች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው “ሰላምም ጦርነትም የሌለበት” ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል፡፡
የእርስ በርስ አለመተማመን የዳግም ግጭት ስጋትን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል ያለው ኢሰመጉ፤ በስምምነቱ መሠረት መተግበር ነበረባው ሲል ከዘረዘራቸው ጉዳዮች መካከል፤ የቀድሞ ታጋዮችን ትጥቅ ሙሉ በሙሉ የማስፈታት፣ የመበተንና የማቋቋም ሂደት መጓተት፣ ኤርትራን ጨምሮ በትግራይ የሚገኙ እና ሌሎች ኃይሎች ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አለመውጣት እንዲሁም የተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለስ ይገኙበታል፡፡
አሁን ባለው ያልተረጋጋ የደህንነት ሁኔታ ውስጥ በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ወታደራዊ ይዘት ያላቸው ዝግጅቶች፣ ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች እና የሚዲያ ዘመቻዎች እንዳሳሰበው ጉባኤው ገልጿል፡፡
“መሰል እንቅስቃሴዎች ያለፈው ጦርነት ካስከተለበት ዳፋ ጨርሶ ያልተላቀቀውን የክልሉን ሕዝብ ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጫና እና ለዳግም ስቃይ የሚዳርግ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል” ብሏል፡፡
ኢሰመጉ በመግለጫው “የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል እና አካባቢው ያለውን ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መስራት አለበት” ሲል አሳስቧል፡፡
እንዲሁም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ስጋት ውስጥ ከሚከቱ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ ጉባዔው ጥሪ አቅርቧል፡፡