“የነጻ መሬት ታጣቂዎች በትግራይ ሰራዊት ላይ ጥቃት ሰነዘሩ” ሲል የትግራይ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ገለፀ።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 25/11/2017፡ የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ትላንት ምሽቱ ባወጣው መግለጫ “ሓራ መሬት” በሚጠሩት የዓፋር መሬት ውስጥ የሚገኙት ታጣቂዎች ምላዛት በተባለው አካባቢ በሰፈረው የትግራይ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሰዋል ሲል ከስሷል።
ቢሮው በአካባቢው በሚገኘው የትግራይ ሰራዊት ላይ በተፈጸመ ጥቃት አንድ አባል መሞቱን አስታውቋል። ረቡዕ ሐምሌ 23/2017 ዓ.ም. በተፈጠረው ግጭት የተገደለው የትግራይ ኃይሎች አባል ዓንዳይ ክንደያ የተባለ መሆኑንም ገልጿል።
ትግራይ ክልል ከአፋር ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱ የሚነገርላቸው እና በተለምዶ “ሓራ መሬት” (ነጻ መሬት) ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች፣ ከትግራይ ኃይሎች ተነጥለው የወጡ ናቸው።
እነዚህ ታጣቂዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ እና ድርጅቱን የሚደግፉ የትግራይ ኃይሎች አዛዦች ከሥልጣን ለማስወገድ ወደ አፋር ክልል ሄደው መደራጀታቸውን ይናገራሉ።
በቅርቡ ራሳቸውን ‘የትግራይ ሰላም ኃይል’ ብለው የሰየሙት እነዚህ ታጣቂዎች በደቡብ ምሥራቅ በኩል ከትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።
መግለጫው አክሎም ‘በነጻ መሬት’ ስም እያሳሳቱ ያሉት ታጣቂዎች፣ “በውጭ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው እና በስምረት ፓርቲ እየተመሩ የትግራይ ተወላጆች እርስ በርስ እንዲጋጩ እያደረጉ ነው” በማለት ከስሷል።
ስምረት ፓርቲ በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ በሆኑት በአቶ ጌታቸው ረዳ እና በሌሎች የቀድሞ ህወሓት አባላት የተመሠረተ አዲስ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው።
ይሄንን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ለሊቱን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በሰጡት መልስ፣ ቢሮው “የትግራይን ኅልውና አደጋ ላይ የሚጥል የወንጀል መረብ አካል ነው” በማለት በገንዘብ ማጥፋት ወንጀል ከስሷል።
አቶ ጌታቸው በክልሉ ሰላማ እና ፀጥታ ቢሮ በእሳቸው እና በአዲሱ ፓርቲያቸው ላይ የተሰነዘረውን ክስ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ‘ስምረት ወታደር እና ገንዘብ የለውም በማለት በግጭቱ ውስጥ እጁ እንደሌለበት አስተባብለዋል። አቶ ጌታቸው ስምረት ፓርቲ ሰራዊት የለውም ቢሉም የፓርቲው አመራር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ አማረ ግን አንድ ወቅት ከሪእዮት ሚድያ በነበራቸው ቆይታ ሰራዊት እንደ አዲስ እያደራጀን ነው ማለታቸው ይታወሳል።
የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በመግለጫው ላይ በአላማጣ ከተማ ባለፈው ሳምንት በአንድ ቤተሰብ ላይ ለተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ የፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂ መሆናቸውንም አመልክቷል።
ቢሮው፣ በአካባቢው የተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች ቢገኙም አላማጣ ከተማ በኮማንድ ፖስት ስር መሆኗን እና ”የፌደራል መከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አካባቢውን የማስተዳደር ኃላፊነት” እንደወሰዱም ገልጿል።
በአላማጣ ከተማ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም ሰለሞን አያሌው በተባሉ ባለሀብት ቤተሰብ ላይ በደረሰ ጥቃት የሁለት ልጆች ሕይወት ሲያልፍ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።