በትግራይ ቆላ ተምቤን ወረዳ ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱ ተገለፀ።
በወረዳው እስካሁን 20 ሰዎች እና በርካታ እንስሳት መሞታቸው የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን አስታውቋል።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 24/11/2017፡ በቆላ ተምቤን ወረዳ በተከሰተው ድርቅ ህፃናትና አረጋውያን ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ ሲሆን በርካታ እንስሳትን በየቀኑ እየሞቱ እንደሆኑ ተገልጿል።
የወረዳው ኢኮኖሚ ዘርፍ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በወረዳው ያቔር ቀበሌ ብቻ 184 ላሞች፣ 900 አህዮች፣ ከ4,500 በላይ በጎች፣ ከ13,000 በላይ ፍየሎች እና 200 ቀፎዎች በዝናብ እጥረት እና በመኖ ችግር መሞታቸወን በመሟጠጡ አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም አረጋውያንና ህጻናት እብጠትና ሌሎችም የድርቁ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
650 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ያልተዘራ እና 50 ሄክታር የተዘራ ሰሊጥ ሳይበቅል መቅረቱን ተመላክቷል።
ከያቄር ጣቢያ ባሻገር በአጎራባች ጣቢያዎች እንደ ሽሉም እምኒ፣ ሚትሻ ወርቂ፣ ዘለቀሜ፣ አረና፣ ነዋይ፣ ጮሞ፣ ደደረ እና ስምረት ጉያ መንደሮች ተመሳሳይ ችግሮች ተስተውለዋል።
በዝናብ ምክንያት ከ900 ሄክታር በላይ መሬት እንዳልተዘራም የተገለፀ ሲሆን አስቸኳይ እርዳታ ከተለያዩ የመንግስት ኤጀንሲዎች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ቢጠይቁም እስካሁን አፋጣኝ ምላሽ እንዳልተሰጠው ተገልጿል።
የትግራይ ተወላጆች፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ኤጀንሲዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የያቄር ጣቢያ ህዝብ አሳሳቢ ሁኔታ ተረድተው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ተጠይቋል።