ካናዳ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ አስታወቀች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 24/11/2017፡ ይህም ከፈረንሳይና ታላቋ ብሪታኒያ በመቀጠል ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ያስታወቀች አገር ያደርጋታል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በመጪው መስከረም ፍልስጤምን በአገርነት እውቅና እንደሚሰጡ ገልጿል።
ካናዳ ይህንን ማስታወቋን ተከትሎ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና እንሰጣለን ያለች ሶስተኛዋ የቡድን ሰባት አባል አገር ሆናለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ዕውቅና በዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው ፤ የፍልስጤም አስተዳደር በሚቀጥለው ዓመት ያለ ሐማስ ምርጫ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።
ወደ 200 የሚጠጉ የቀድሞ የካናዳ አምባሳደሮች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንዲሰጡ ፊርማቸውን ባኖሩበት ደብዳቤ ጠይቀዋል።
“ፍልስጤማውያን በየቀኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጠነ ሰፊ መፈናቀል፣ ማንንም የማይለይ የቦምብ ድብደባ እንዲሁም በጋዛ ሰላማዊ ዜጎች እየተራቡ እና በዌስት ባንክ ጽንፈኛ ሰፋሪዎች በሚያደርጓቸው ከፍተኛ ጥቃቶች የካናዳን መርሆች ተዘንግተዋል” ብለዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየት የተሰማው ዩናይትድ ኪንግደም እስራኤል ለተኩስ አቁም እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች የማትስማማ ከሆነ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና እንሰጣለን ካሉ በኋላ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤም አገርነት እውቅና እስራኤል ማሟላት ባለባት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ከዚያ ቀደም ብሎ ግን ፈረንሳይ በመጪው መስከረም ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እሰጣለሁ ማለቷ ይታወሳል።