
ኢትዮ ሞኒተር፡ 24/11/2017፡ ዓለምአቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅን ውድቅ እንዲያደርግ አሳስቧል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ረቂቅ ህጉ “ለፌደራል መንግስት ሰፊ ስልጣን የሚሰጥ እና የሲቪክ ምህዳርን በእጅጉ የሚገድብ ነው” ሲልም አስጠንቅቋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ረቂቁን እንዲያወግዙ እና ማንኛውም የህግ ማሻሻያ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ደረጃዎች ጋር መጣጣም እንዳለበት አሳስቧል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው አዲስ ጽሑፉ እንዳለው፤ “የኢትዮጵያ ሕግ አውጪዎች የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ማሻሻያ ረቂቅን ውድቅ ማድረግ አለባቸው” ብሏል።
ረቂቅ አዋጁ “ለአስፈጻሚው አካል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመገደብ ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ ነው” ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ “ገና ለፓርላማ ያልቀረበውን ይህን ረቂቅ ሕግ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች እንዲቃወሙት አሳስቧል”።
ሂውማን ራይትስ ዎች፤ በሰኔ ወር 2018 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው 7ኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ቀደም ብሎ የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ የፌደራል መንግስት፤ “በአስተዳደር እና ከምርጫ ጋር በተያያዙ ስራዎች ላይ ለተሰማሩ ቡድኖች የሚሰጠውን የውጭ የገንዘብ ድጋፎችን ለመከልከል፣ እንዲሁም “የሀገር ደህንነት” ተብሎ በቀረበው ግልጽ ያልሆነ ምክንያት ላይ ተመስርቶ የህግ ክትትል እና ይግባኝ የማለት መብት ሳይሰጣቸው ድርጅቶችን ከመመዝገብ እንዲከለክል እና እንዲያግድ” ያስችለዋል ብሏል።
የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር፤ “በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ሕግ ላይ የቀረቡት ማሻሻያዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት የመጡትን ለውጦች የሚያፈርስ እና ወደ ኋላ የሚመልስ ነው” ብለዋል።
አክለውም ረቂቅ ህጉ ለሲቪል ማህበራት ተሳትፎ እና ለመብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ከባድ ስጋት እንደሚፈጥርም አስጠንቅቀዋል።
“ማሻሻያ ረቂቁ የቀረበው መንግሥት በሲቪል ማኅበራት እና በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ላይ የሚያደርገው ጫና እየጨመረ ባለበት እና በአገር ውስጥ የሲቪክ ምኅዳሩ እየጠበበ ባለበት ወቅት መሆኑን” የመብት ተሟጋች ድርጅቱ አመልክቷል።