ታላቋ ብሪታኒያ እስራኤል ቅድመ ሁኔታዎችን ካላሟላች ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና እንደምትሰጥ አስታወቀች።

ኢትዮ ሞኒተር፡ 23/11/2017፡ ታላቋ ብሪታኒያ እስራኤል “በጋዛ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ለማስቆም ተጨባጭ እርምጃዎችን” ካልወሰደች በመስከረም ወር ለፍልስጤም እውቅና እንደምትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስተር ኪር ስታርመር ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነትን ማድረግ፣ የሁለት አገር መፍትሄ የሚያመጣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ አቅርቦቱን እንደገና እንዲጀምር መፍቀድን ጨምሮ፣ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባት፤ አለዚያ እንግሊዝ እርምጃውን በመስከረሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ትወስዳለች ብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እርምጃው “ለሐማስ አስከፊ አሸባሪነት ሽልማት ነው” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከዚህ ቀደም ለፍልስጤም እውቅና መስጠት እንደ የሰላም ሂደት አካል ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ጊዜ ሊደረግ ይገባል ሲል ተናግሯል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስዱ ከራሳቸው የፓርላማ አባላት ጭምር ጫና እየደረሰባቸው ነው።
አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ኪር፣ እቅዱን አሁን እያስታወቁ ያሉት በጋዛ ስላለው “ትዕግሥት የሚፈትን ሁኔታ” እና “የሁለት መንግሥታት የመፍትሄ ዕድሉ እየቀነሰ ነው” የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው።
ባለፈው ሳምንት ፈረንሳይ በመስከረም ወር ለፍልስጤም መንግሥት በይፋ እውቅና እንደምትሰጥ አስታውቃለች።